በኢመደበኛ ፍልሰት ወደ ብሪታንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በቶሎ እንዲመለሱ ሊደረግ መሆኑ ተሰማ

ትናንት ለጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይቬት ኩፐር፣ የደገሃቡር-ቀብሪደሃር ፕሮጀክት የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ትናንት ከመንግሥት ጋር ተፈራርመዋል።

ሚንስትሯ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ኢትዮጵያዊያን ወደ ብሪታንያ የሚያደርጉትን ኢመደበኛ ፍልሰትን በመግታት ዙሪያ እንደሚወያዩ ከጉብኝታቸው ቀደም ሲል ባወጡት መግለጫ ገልጠው ነበር።

የሥራ እድሎች ለመፍጠር አጋርነቶችን መፈጸም ፍልሠተኞች አገራቸውን እንዳይለቁ እንደሚረዳ በመግለጫቸው የጠቀሱት ኩፐር፣ በሌላ በኩል ሕግጋትን ማጠናከር የሰው አዘዋዋሪዎችን እንቅስቃሴ ለመግታትና ብሪታንያ ውስጥ የመቆየት ሕጋዊ መብት የሌላቸውን ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ወደ አገራቸው በቶሎ እንዲመለሱ እንደሚረዳ ጠቅሠዋል።

ሚንስትሯ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ትናንት ከተወያዩ በኋላ፣ ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ያስችላሉ የተባሉትን የሁርሶ- አይሻ እና የደገሃቡር-ቀብሪደሃር የኢነርጂ ፕሮጀክቶች የኃይል ማስተላለፊያ ለመገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተፈራርመዋል።

ብሪታንያ ለኢትዮጵያ የምትሠጠው የ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነትም ተፈርሟል።