የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አባሉ እና በቅርቡ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የተዋሃደው የቀድሞው ተቃዋሚ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት ዮሐንስ ተሠማ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ ከመሠረቱባቸው የሽብር ክሶች ነጻ ናቸው ሲል ውሳኔ ሠጠ።
በአሶሳ ከተማ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ተከሳሹን ዛሬ ከሽብር ክሶች በነጻ ያሠናበታቸው፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ በቂ ማስረጃና ምስክሮች ማቅረብ አልቻለም በማለት መኾኑን በችሎቱ የታደሙ የተከሳሹ የቤተሰብ አባላት ለዋዜማ ተናግረዋል። ሆኖም ዓቃቤ ሕግ ወደፊት ምስክሮችን ሲያቀርብ ክሱን ማንቀሳቅስ እንዲችል ተፈቅዶለታል።
በዮሐንስ ላይ የቀረቡት ተደራራቢ ክሶች፣ “ለኦነግ-ሸኔ አባል መረጃ መስጠት፤ “የክልሉን ሕገመንግሥት ለመናድ መንቀሳቀስ”፤ “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር” እና “የመተከል ዞንን ወደ አማራ ክልል ለማካለል ማሴር” የሚሉት ናቸው፡፡ ዮሐንስ ቀደም ሲል ከአሶሳ ከተማ የመሬት ሊዝ ጋር በተያያዘ ፈጸሙት በተባለ ወንጀል የ6 ዓመት እስር እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡
ዮሃንስ ባለፈው ዓመት ለእስር የተዳረጉት፣ በክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት ላይ ምክር ቤቱ “ኢ-ሕገመንግሥታዊ” በሆነ ሁኔታ ያደረገውን ማሻሻያ በመቃወም የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ትርጉም እንዲሠጥበት ከሁለት ጓዶቻቸው ጋር አቤቱታ ባቀረቡ ማግስት ነበር።