የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ስምረት ፓርቲ፣ “ኋላቀር” ሲል የጠራው የሕወሃት ቡድን ከባድ መሳሪያዎችን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በማስጠጋት ተኩስ ከፍቷል በማለት ከሠሠ።
ስምረት፣ ሕወሃት አፋር ክልልን እና የጎንደር አካባቢን ያካለለ “መጠነ-ሰፊ” ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅቱን ጨርሷል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ከሷል። በቅርቡ በመንግሥት እና በሕወሃት ኃይሎች መካከል ጠለምት ላይ ግጭት መካሄዱን የጠቀሠው ፓርቲው፣ ቡድኑ ጦርነት የከፈተው የትግራይን “የግዛት አንድነት” እና “የተፈናቃዮችን መመለስ ጉዳይ” እንደ ሽፋን በመጠቀም ነው ብሏል።
ቡድኑ ቀድሞ የቀበራቸውንና የደበቃቸውን ከባድ መሣሪያዎች በማውጣት ግጭት ጀምሯል በማለት ጭምር ፓርቲው የከሠሠ ሲኾን፣ የቡድኑ እንቅስቃሴ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት “ሙሉ በሙሉ” በማፍረስ የሚያካሂደው ነው ሲል በመግለጫው አካቷል። የሕወሃት ቡድን ይህን ጦርነት የጀመረው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተሰልፎ ነው በማለትም ፓርቲው ከሷል. ሳልሳይ ወያነ እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲም፣ ዓለማቀፍ አጋሮች በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል መጠነ ሰፊ ግጭት እንዳይከሠት ፍጥጫው እንዲረግብ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።