የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ የሱፍ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ሕወሃት መተማመንን ከሚሸረሽሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እና እስካሁን ያልተፈቱ ጉዳዮችን በገንቢ ንግግር እንዲፈቱ ጠየቁ።
የሱፍ፣ በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሠቱ ክስተቶች በጥልቅ እንዳሳሰቧቸው እኩለ ቀን ላይ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተሉ መሆኑን የጠቀሱት የሱፍ፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ያስገኛቸውን እድሎች መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ቡድን አሁንም በሁለቱ ወገኖች መካከል ንግግር እንዲካሄድ ለማመቻቸትና መተማመንና ትብብር እንዲጎለብት ለማስቻል ዝግጁ መሆኑንም የሱፍ አረጋግጠዋል።