ከሳንጃ ውግ እስከ ክላሽ ጨበጣ ውጊያና ቦምብ ውርወራ የደረሰው ከባዱ ትንቅንቅና የተሰበረው የጠላት ምሽግ!

በምስራቅ ዐምሓራ ቀጠና በተሁለ ድሬ ወረዳ ከሐይቅ ከተማ በቅርብ ርቀት ልዩ ስሙ ቆሎ ባቄላ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ላይ የሚገኘውና ከቦታ አቀማመጡ ጋር ተዳምሮ በመዘመናዊ መንገድ ተሰርቶ የነበረው የአገዛዙ ወታደራዊ ምሽግ በፋኖ ቦምብ ድርምስምሱ ወጥቷል።

በምሽጉ ውስጥ የነበሩ በርካታ ወታደሮች የእሳት እራት ሆነው ሲቀሩ፡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሸሹ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካቶች ደግሞ ገደል ገብተው አልቀዋል።

በአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒሊክ ዕዝ ልጅ እያሱ ኮር 24ኛ ክ/ጦር ጥር 19 ለጥር 20/2018 ዓ/ም አጥቢያ ሌሊት በፈፀሙት ታአምራዊ ኦፕሬሽን የጠላትን አከርካሪ በመስበር ታላቅ ድል መጎናፀፋቸውን የመረብ ሚዲያ የምስራቅ ዐምሓራ ቀጠና ዘጋቢዎች ለማረጋገጥ ችለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ልዩ ቦታው ቆሎ ባቄላ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በነበረው የአገዛዙ ወታደሮች ምሽግ ላይ ነው መብረቃዊው እርምጃ የተወሰደው።

ከቦታው መልካአ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር ተዳምሮ በመዘመናዊ መንገድ ተሰርቶ የነበረው የአገዛዙ ወታደሮች የኮንክሪት ምሽግ ነው “ተናዳፊዎቹ” በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት በልጅ እያሱ ኮር ስር የ24 ክ/ጦር ፋኖዎች ትናንት አጥቢያ ለሊቱን የጥቃት ዶፍ አውርደውበት ድርምስምሱን ያወጡት።

የፋኖ አባላቱ የጥይት ካዝናቸውን እንዳነገቡና የብሬን ሸንሼናቸውን ልክ እንደመቀነት በወገባችው ደግድገው በደረታቸው እየተሳቡ በጠላት ምግሽ ተወርውረው በመግባት በቅድሚያ የምሽጉ ዋርድያዎችን በድምፅ አልባው ሳንጃ ካጋደሙ በኋላ በምሽጉ ውስጥ የነበሩ ወታደሮችን ጭዳ እንዳደረጓቸው የመረብ ሚዲያ የቀጠናው ዘጋቢ ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።

የሳንጃ ትንቅንቅን ጨምሮ የክላሽ ጨበጣ ውጊያው የተካሄደው በድቅድቅ ጨለማ በመሆኑ የተገደሉ የአገዛዙ ወታደሮች ቁጥር በውል ባይታወቅም ነገር ግን በርካቶች የአፈር ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል።

በዚህ መብረቃዊ ኦፕሬሽን ከፋኖ ሳንጃና አፈሙዝ ለማምለጥ ሲሸሹ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካቶች ደግሞ ገደል ገብተው መሞታቸው ነው የታወቀው።

የፋኖ አባላቱ፡ ጠላት አይደፈሬ በሚል ሲመካበት የነበረውን ምሽግ ሰዓታትን ባልፈጀ ውጊያ ድርምስምሱን በማውጣት በርካታ ወታደሮችን ከደመሰሱ በኋላ 15 ክላሽንኮቭ መሣሪያዎችን ከነ ተተኳሾቻቸው እንዲሁም ሌሎች ለትግሉ አስፈላጊ የሆኑ ወታደራዊ ግብአቶችን ከበርካታ ወታደሮች ጋር ማርከው በድል ታጅበው ቀጠናውን ለቀው መውጣታቸውን ነው ጣቢያችን መረብ ሚዲያ ለማረጋገጥ የቻለው።

ከሐይቅ ከተማ በውስን ኪሎሜትሮች እርቀት ቆሎ ባቄላ አከባቢ በነበረው ምሽግ ላይ ከእኩለ ለሊት ጀምሮ በፋኖ የተከፈተውን ጥብቅ እርምጃ የሰሙ በሐይቅ ከተማ የነበሩ የአገዛዙ ምንጣፍ ጎታች ካድሬዎች አንዳንዶች የለሊት ፒጃማ እንደለበሱ፡ አንዳንዶች ደግሞ በቁምጣና ፓንት ብቻ ሆነው በደረቅ ለሊት ወደ ደሴ ከተማ መሸሻቸው ነው የተነገረው።

በከተማዋ መኃል ሸሙሳ ተብሎ በሚጠራው ተራራማ ስፍራ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ቀሪው የአገዛዙ ኃይል፡ ባጠመደው ከባድ መሣሪያ ቆሎ ባቄላ ለነበሩ ጓዶቹ ሽፋን ሲሰጥ ያደረ ቢሆንም፡ ነገር ግን የአንድ ወታደርን ሕይወት ሳይታደግ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” ሆኖ ቀርቷል።