ሀገር አፍራሹ የብልፅግና ቡድን በአፋር ሓራ መሬት ብሎ በጠራው አከባቢ እያደራጀው በሚገኘው ታጣቂ ኃይል እና በአፋር ሕዝብ መካከል ከባድ ግጭት ተቀስቅሷል።

ሀገር አፍራሹ የብልፅግና ቡድን በአፋር ሓራ መሬት ብሎ በጠራው አከባቢ እያደራጀው በሚገኘው ታጣቂ ኃይል እና በአፋር ሕዝብ መካከል ከባድ ግጭት ተቀስቅሷል።

ሕዝቡ አፋር የጦርነት ቀጠና አይደለችም፡ በአስቸኳይ ክልላችንን ለቃችሁ ውጡ በሚል ወደ አደባባይ በመውጣት ቁጣውን የገለፀ ሲሆን፡ ታጣቂዎቹ ደግሞ በሕዝቡ ላይ የዘፈቀደ ተኩስ በመክፈት በርካታ ንፁኋንን ማቁሰላቸው ታውቋል።

በአፋር ሐራ መሬት ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በብልፅግና እገዛ እራሳቸውን እያደራጁ በሚገኙት በእነጌታቸው ረዳ እንዲሁም በእነፃድቃን ገብረተንሳይ ታጣቂዎች እና በአፋር ሕዝብ መካከል ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረ ከባድ ግጭት መቀስቀሱን ምንጮች ገልፀዋል።

በክልሉ ኪልበቲ ረሱ ዞን በርሃሌ ወረዳ ስር በምትገኘው ቡሬ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ  የተጀመረው ግጭቱ አሁን ላይ አድማሱን አስፍቶ ታጣቂዎቹ በሰፈሩባቸው በሁሉም አከባቢዎች ተዳርሷል ነው ያሉት ምንጮቻችን።

ብልፅግና ከአማራ ሕዝብ ጋር በሚያደርገው ውጊያ እንዲያግዙት ወዲህ ደግሞ ሕወሓትን ለሁለት ለመክፈል ሲል ስንቅም ትጥቅም ከቤተመንግስት እየሰፈረላቸው በአፋር ክልል ሓራ መሬት በተባለ አከባቢ እያሰለጠናቸው የሚገኙት የነጌታቸው ረዳ ታጣቂዎች ሴት ከመድፈርና የቀንድ ከብት ከመዝረፍ ጀምሮ በአፋር ሕዝብ ላይ ከባድ ሰብአዊ ግፍ እየፈፀሙ መክረማቸው ሲነገር ቆይቷል።

አገዛዙ ከወራት በፊት በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ጋዝጊብላ ወረዳ ላይ ከፋኖ ጋር ባደረገው ውጊያ የሓራ መሬት ታጣቂዎች ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው ወደ ውጊያ ገብተው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከወደ ፋኖ በተወሰደባቸው የፀረ መከላከልና የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከባድ የሆነ ሰብአዊና ቁሣዊ ኪሳራ መከናነባቸውን በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም።

አገዛዙ በወቅቱ ለመከላከያ ሰራዊቱ እገዛ እንዲያደርጉለት ታጣቂዎቹን በጭፍራና በቆቦ አድርጎ በኮረም በኩል በማስገባት አሰልፏቸው የነበሩት ናቸው ከባድ ኪሳራ የደረሰባቸው።

በወርሃ መስከረም 2018 ዓ/ም በምስራቅ ዐምሓራ ቀጠና በተካሄደው በዘመቻ አባናደው ሽንፈትን ከእግር ጥፍሩ እስከ እራስ ፀጉሩ የተከናነበው ብልፅግና፡ “የሕወሓት ታጣቂዎች ከፋኖ ጋር ተሰልፈው ወጉኝ” የሚል የበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ ለመስራት ሓራ መሬት ከሚገኙ የነጌታቸው ረዳ ታጣቂዎች በመመልመል ምርኮኛ አስመስሎ ቃለመጠይቅ ማድረጉን በወቅቱ ጣቢያችን የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወቃል።

እነዚህ የሓራ መሬት ታጣቂዎች እየተደራጁ በሚገኙበት የአፋር ክልል አከባቢ ንፁኋኑን በመግደልና ሴት በመድፈር የሚፈፅሙት ግፍ ከቀን ወደቀን እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፡ ይሄንን መሸከም የከበደው የአፋር ሕዝብ በቃችሁ ብሎ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ወጥቷል።

ከትግራይ ምስራቃዊ አቅጣጫ ባሉ የአፋር ክልል አከባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት እነዚህ የእነጌታቸው ረዳ ታጣቂዎች ከአፋር ሕዝብ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለማፈን ባዶ እጁን በወጣ ሕዝብ ላይ ተኩስ በመክፈት በርካታ ንፁኋንን ያቆሰሉ ሲሆን፡ ይህ ድርጊታቸውም ግጭቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲደርስ አድርጎታል ብለዋል   ምንጮች።

አሁን ላይ ሕዝቡ “አይናችን እያየ ቁጭ ብለን አንሞትም በሚል” ከድንጋይ ጀምሮ ዱላና ቆንጨራ በመያዝ ታጣቂዎቹን ፊትለፊት የተጋፈጣቸው ሲሆን፡ ታጣቂዎቹም በምላሹ የተኩስ አፀፋ እየወሰዱ ይገኛሉ።

ከትናንት በስቲያ ጥር 18/2018 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በርካታ የታጣቂ ኃይሉ ንብረቶች በአፋር ሕዝብ ወድመዋል