ኢትዮጵያ የሕጻናት የወንጀል ተጠያቂነት የእድሜ ገደብን ከ9 ዓመት ከፍ እንድታደርግ ተጠየቀ

ኢትዮጵያ የሕጻናት የወንጀል ተጠያቂነት የእድሜ ገደብን ከ9 ዓመት ከፍ እንድታደርግ የተመድ የሕጻናት መብት ኮሚቴ ትናንት የኢትዮጵያን የሕጻናት መብት ይዞታ በገመገመበት ወቅት ጠየቀ። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፣ መንግሥት በጥናት በሚያገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ የእድሜ ገደቡን ለማሻሻል ዝግጁ መኾኑን በመድረኩ ላይ በሠጠው ምላሽ ገልጧል። አንድ የኮሚቴው ባለሙያ፣ ሕጻናት ጭምር ሰላማዊ ሰዎች በተሳተፉባቸውና ሕይወት በጠፋባቸው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ “ያልተመጣጠነ ኃይል” በተጠቀሙ የጸጥታ አካላት ላይ ምርመራ ተደርጓል ወይ? በማለት ጠይቀው ነበር። ልዑካን ቡድኑ፣ በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ኃይል መጠቀምን ለመከላከል ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱን ጠቅሶ፣ ባንድ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተይዘው ታስረዋል የተባሉትን ልጃገረድ ሕጻናት ጉዳይ ግን አጣራለሁ ብሏል። ከሕጻናት የጾታ ጥቃት አንጻር፣ በብሄራዊ ደረጃ “የጾታ ጥቃት ፈጻሚዎች መዝገብ” በቅርቡ ተግባር ላይ እንደሚውል ልዑካኑ ገልጧል። መንግሥት ምን ያህል በጀት ለሕጻናት ተኮር ሥራዎች እንደመደበ ለቀረበው ጥያቄም፣ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቱ ሦስት በመቶው ተመድቧል ሲል ልዑካኑ ምላሽ ሠጥቷል።