አብዱራህማን መሃዲ የሚመሩት የኦብነግ ክንፍ እና ሁለት የሶማሌ ክልል ተቃዋሚ ድርጅቶች በቅርቡ ያቋቋሙት ጥምረት፣ በክልሉ በአፍዴር፣ ሸበሌ እና ዳዋ ዞኖች የተከሠተው ድርቅ “ሰብዓዊ ቀውስ” አስከትሏል አለ። ሰብዓዊ ቀውሱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ብቻ የተከሠተ አይደለም ያለው ጥምረቱ፣ የመንግሥት “የዝግጁነት ማነስ”፣ “የሰብዓዊ እርዳታ ብክነት” እና “የዘላቂ እቅድ አለመኖር” ጭምር የሰብዓዊ ቀውሱ ምክንያት ናቸው ሲል የክልሉን መንግሥት ወቅሷል። የሰብዓዊ ቀውሱ ሰለባዎች “አስቸኳይ” ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥምረቱ የጠየቀ ሲኾን፣ የዕርዳታ አቅርቦቱም “በገለልተኛ” አካል ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ብሏል። በሦስቱ ዞኖች ተከስቷል ላለው ሰብዓዊ ቀውስ በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ሶማሌዎች ዕርዳታ እንዲያሰባስቡ የጠየቀው ጥምረቱ፣ ኾኖም ዕርዳታው በመንግሥት በኩል ሳይኾን “በታማኝ” የረድኤት ድርጅቶችና “በማኅበረሰብ መዋቅሮች” በኩል ብቻ በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ጥሪ አቅርቧል።