የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር,፣ በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ላይ የሚፈጸሙ የባይነ መረብ ጥቃት በእጅጉ ተስፋፍቷል በማለት አስጠነቀቀ። የበይነ መረብ ጥቃት ፈጻሚዎቹ በአገሪቱ የሚካሄዱ የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን፣ ዓለማቀፍ መድረኮችንና የበይነ መረብ ስብሰባዎችን ለሐሰተኛ ድርጊቶቻቸው መጠቀሚያ እያደረጓቸው እንደሚገኙ ተቋሙ ገልጧል። ተቋሙ፣ ጥቃት ፈጻሚዎች የግለሰቦችንና ተቋማትን የባንክ ሂሳቦች ለመመዝበር፣ የግለሰቦችን የግል መረጃዎች ለመመንተፍ እና የዲጂታል ደኅንነትን ለማናጋት “በተቀናጀ” መልኩ እየሠሩ ስለመኾኑም በክትትልና ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል። የበይነ መረብ ጥቃቶቹ የሚፈጸሙት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጣቸውን “ተፈላጊ” እና “ወቅታዊ” ጉዳዮች መነሻ በማድረግ በተዘረጋ “ስልታዊ የማታለያ ዘዴ” ነው ያለው ተቋሙ፣ የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ከማይታወቁ ወይም ካልተረጋገጡ አድራሻዎች በዋትሳፕ፣ ቴሌግራምና በሌሎች የዲጂታል የመገናኛ ዘዴዎች የሚላኩላቸውን የድረገጽ መረጃዎች እንዳይከፍቱና አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሷቸው ወዲያውኑ “ሪፖርት” እንዲያደርጉም አሳስቧል።