የአብይ አህመድ ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎችን ጥያቄዎች ማጣጣሉን ቀጥሏል

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ኢሕአፓንና መኢአድን ጨምሮ ስምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከእጩዎች የዲጂታል ምዝገባ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ያቀረቡትን ቅሬታ “አግባብነት የሌለው” እና “የእጩዎችን ምዝገባ ከማስተጓጎል” ያለፈ ምንም ጥቅም የሌለው ነው በማለት አጣጣለ።

ቦርዱ፣ ከብሄራዊ መታወቂያ ውጭ ለቀጣዩ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባ የጠየቀው አዲስ “ሰነድ” ወይም “ማስረጃ” እንደሌለ ለፓርቲዎቹ ቅሬታ በሠጠው ምላሽ ገልጧል።

ከከተሞች ውጭ ያሉ እጩዎች ለምዝገባ የትውልድ የምስክር ወረቀት ማቅረብ ካልቻሉ ሲወለዱ በአካል የነበረ የዓይን ምስክር ማቅረብ እንዳለባቸው ቦርዱ ግዴታ አስቀምጧል በማለት ፓርቲዎቹ ያቀረቡት ቅሬታ ስህተት አለበት ያለው ቦርዱ፣ የውልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ ያልቻለ እጩ በሚወዳደርበት የምርጫ ክልል መወለዱን በሚያውቁ የሰው ምስክሮች ማረጋገጥ እንደሚችል አማራጭ ማስቀመጡን አብራርቷል።

ቦርዱ፣ እጩዎች ከወከሏቸው ፓርቲዎች እውቅና ውጭ ራሳቸውን ከእጩነት ማግለል እንዲችሉ ተፈቅዷል የተባለው ቅሬታም ከአሠራሩ ውጭ የኾነ ቅሬታ ነው ሲል አስተባብሏል።