መሰንበቻውን የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡ የዋና ዳይሬክተሯ ጉብኝት ዋና ዓላማ፣ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ወዲህ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዞ ያለበትን ደረጃ መገምገምና ተጨማሪ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን መርሐ ግብር ይፋ ካደረገ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ብልፅግና ለማምጣት የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለመፍጠር ደፋ ቀና እያለ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል፡፡ አይኤምኤፍም ከፖሊሲው ትግበራ ወዲህ ኢኮኖሚው አስተማማኝ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው የሚገልጸው፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው የሕዝቡ ኑሮ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ የፖሊሲ ትግበራው ይዟቸው የመጡትን ተጨማሪ ወጪዎች መቌቌም ተስኖታል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ የምርቶችንና የሸቀጦችን አቅርቦት በማጠናከር የዋጋ ንረትን ለማርገብ ቃል ቢገባም፣ የኑሮ ውድነቱ ብዙዎችን እየደቆሳቸው ነው፡፡ የምግብ ምርቶች፣ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ እንዲሁም የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች ዋጋቸው ወይም ታሪፋቸው ከመጠን በላይ በመጨመሩ ኑሮ ከመጠን በላይ ከብዷል፡፡ የአይኤምኤፍም ሆነ የዓለም ባንክ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ሚዛንን መጠበቅ ካልተቻለ፣ መንግሥት የሚፈልገውን ብድርና ድጋፍ ሲያገኝ ለዜጎች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ የሚባሉ ድጎማዎች እየቀሩ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ መንግሥት ለሠራተኞቹ ደመወዝ ቢጨምርም ሆነ የሴፍቲኔት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቢያቀርብም፣ የምርቶች አቅርቦት ካልተስተካለና የዋጋ ንረት ካልረገበ ጉዳቱ ይቀጥላል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የዜጎች ገቢ ከወጪያቸው ጋር ስለማይጣጣም፣ ኑሮ የከበዳቸው ሰዎች ምፅዋት ልመና ወደ ጎዳና እየወጡ ነው፡፡
ሌላው ትልቁ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ጦርነት ነው፡፡ ከሌሎች መለስተኛ ከሚባሉ በጣም በርካታ ግጭቶች በተጨማሪ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች ምርት የሚታፈስባቸው መሬቶች እንዳይታረሱ፣ የተመረተ ካለም በአግባቡ ወደ ገበያ እንዳይወጣ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ ወይም እንዲቆሙ፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚ ዕድገት በተቃራኒ ለውድመት ምክንያት መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ሰላም ጠፍቶ የምርቶችና የአገልግሎቶች ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር የዜጎች ገቢ ግን ባለበት እየሄደ ነው፡፡ ጦርነት የአምራች ዜጎችን ሕይወትና የአገር ሀብት እንደ ሰደድ እሳት ይባላል፡፡ ለአገር ልማት ሊውል የሚገባውን የሰው ኃይል፣ ሀብት፣ ጊዜና ኢነርጂ ያባክናል፡፡ ጦርነት የሚካሄድባት አገር ውስጥ ዕድገት አለ ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ችግሩ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ ለሰላም መስፈን የሚረዱ አማራጮች ሁሉ ታይተው የመፍትሔው መንገድ ይፈለግ፡፡
መንግሥትም ሆነ አይኤምኤፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ወደፊት ይዞት የሚመጣው ውጤት ላይ እንዲተኮር ይፈልጋሉ፡፡ እንደተባለው በጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የሚመራው ኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነት ላይ በስፋት ከተሠራበት ውጤት ሊገኝበት እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ነገር ግን በየቦታው የሚካሄዱ ግጭቶች ቆመው እርሻዎች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የምግብ ማቀነባበሪያዎችና ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያግዙ ሌሎች ዘርፎች በሙሉ ኃይላቸው የሚሠሩበት ዕድል መፈጠር አለበት፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች በስፋት መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ዓይነት ማዕድናት ለገበያ መቅረብ አለባቸው፡፡ ጎብኚ ያጡ የቱሪስት መስህቦች መነቃቃት መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት በስፋት መቀላጠፍ ይኖርበታል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ሚሊዮኖችን እያስጨነቀ ያለው የኑሮ ውድነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይደረግ፡፡ የነገውን ተስፋ ለማየት የሚቻለው ዛሬ እየደረሰ ካለው ጉዳት ማገገም ሲቻል ነው፡፡
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ጥቅም ለማስከበር በሚል ምክንያት በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ሳቢያ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አገሮች የጉዳት ሰለባ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዕርዳታዎች የተሰማራው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)፣ በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ሥራዎቹ እንዲቋረጥ ሲደረግ በጤናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሥራቸውን ማጣታቸው ተሰምቷል፡፡ ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ በምግብና ምግብ ነክ ዕርዳታ ሰጪነት የተሰማሩም ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን መንግሥት በማይሸፍናቸው ፕሮጀክቶች በተሰማራው ዩኤስኤአይዲ፣ እንዲሁም በሌሎች ተመሳሳይ የረድዔት ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችና ስደተኞች ጭምር ዕጣ ፈንታቸው በእጅጉ ያሳስባል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ዕርዳታ ጠባቂዎችን ጭምር የሚያካትት መፍትሔ ካልተገኘ መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡
የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ ምክንያት መካከለኛ ገቢ የነበራቸው ዜጎች የኑሮ ክብደቱን መቋቋም እየተሳናቸው ነው፡፡ ወትሮም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩ ምኑን ከምኑ አያይዘው እንደሚኖሩ ግራ ያጋባል፡፡ ከአይኤምኤፍ ጋርም ሆነ ከዓለም ባንክ ጋር የተደረጉ ስምምነቶች መንግሥት ከሁሉም ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ድጎማ እንዲያነሳ ነው የሚያሳስቡት፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና አላባራ ባለ ጦርነት ኢኮኖሚዋ የደቀቀ አገር ውስጥ፣ የገንዘብ ድርጅቶቹን ፖሊሲ እንደወረደ ማስፈጸም በሰዎች ሕይወት እንደ መፍረድ ይቆጠራል፡፡ የገንዘብ ድርጅቶቹ ፖሊሲ ተግባራዊ የተደረገባቸው በርካታ አገሮች ልምድ የሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረትን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁከት ሲቀሰቀስም በብዛት ተስተውሏል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ጉዳት በመገንዘብ ማስተካከያዎች ያድርግ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚያቃልሉ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ!