ዜና ዕረፍት፣ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ። ቅዱስ ሲኖዶስም “ሥርዓተ ቀብራቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይፈጸማል” ሲል የጠቅላይ ቤተ ክህነት ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለቤተ ክህነት ቴሌቪዥን እንደገለጸው ከሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ሥርዓተ ቀብር ነገ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም በተማሩበት በመነኮሱበት እና ለረጅም ዓመታት ባገለገሉበት በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይፈጸማል።
=====
ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ማን ነበሩ?
=======
+ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በቀድሞ ስማቸው ጸባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው ይባሉ ነበር።
+ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም (የቀድሞው ፀባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው) በደብረ ብርሃን አውራጃ በሚገኘው በእነዋሪ ወረዳ ልዩ ስሙ ከያዱር በዓለ ወልድ በሚባለው ቀበሌ ከአባታቸው ከአቶ ባሳዝነው ወንድም አገኘሁና ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለ ማርያም ማናየ ተወለዱ፡፡
+ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በዚሁ አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ገዳም በመሄድ ፊደል መቁጠር እንደጀመሩ ወደ ሰቃ መድኃኔ ዓለም ገዳም በመሄድ ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍት ከሚያስተምሩት ከታላቁ ምሁር አባት ከመምህር አባ ዘካርያስ ኃይለ ማርያም ዘንድ (ዛሬ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ) ከፊደል ጀምሮ ንባብ ከነቃል ትምህርቱ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም በእሳቸው እየተወከሉ ከሚያስተምሩ ከመምህር አስበ ጸድቅ ወርቅነህና ከአባ ተክለ ሃይማኖት ሀብተ ጊዮርጊስ ዳዊት ተምረዋል፡፡ ከዚያም በመቀጠል በዚሁ ገዳም ቅዳሴ ያስተምሩ ከነበሩት ከመምህር ገብረ ሚካኤል ሥርዓተ ቅዳሴና ሰዓታት ተምረዋል፡፡
+ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በቀድሞ ስማቸው ፀባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ግንቦት ፲፪ ቀን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጎጃም ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ መዐርገ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ በዚሁ በሰቃ መድኃኔ ዓለም ገዳም ከማኅበረ ገዳሙ አንድነት ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉና እያጠናከሩ በዲቁና ሥራ ከልዩ ልዩ ተልእኮ ቀናነት የተላበሰ መንፈሳዊ አገልግሎትን በተገቢው መንገድ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡
+ አሁንም መንፈሳዊ እውቀታቸውን ለማዳበርና ለማካበት ወደ ታላቁ ስመጥር ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ በመሄድ ከታላቁ መንፈሳዊ የድጓ መምህር ከሆኑት ከየኔታ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ጾመ ድጓ ከነቃል ትምህርቱ ተምረዋል፡፡
ይሁን እንጂ እዚሁ ትምህርት ቤት ገበታ ላይ እንዳሉ መን ፈሳዊ የትምህርት ቅናት ስለገፋፋቸውና ስላነሣሣቸው ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሄደው በደንበጫ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅኔ መምህርነት ተመድበው ከሚያስተምሩት ከመምህር ብዙአየሁ አሰጌ ዘንድ ቅኔ እየተማሩ እስከ ሥላሴ ቅኔ ቈጥረዋል፡፡ ከዚያም ወደ በጌምድር ጉዞአቸውን በማቅናት ደራና ፎገራ ከሚባለው አካባቢ በእማሽንኮሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ተቅዋመ ወርቅ ዘንድ ከአንድ ዓመት በላይ ቆይታ በማድረግ የጀመሩትን የቅኔ ትምህርት ተከታትለው ከተቀኙ በኋላ ቀድሞ ወደቆዩበት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ተመልሰዋል፡፡
ከዚያም በመቀጠል በዚሁ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከመምህር ወልደ ገብርኤል ያለው ዘንድ ዝማሬ መዋሥዕት በሚገባ ተምረዋል፡፡ በዚሁ ትምህርት ቤት አቋቋም እየተማሩ እንዳሉ ገዳማዊ ሕይወት ለመኖር በዚሁ ታላቅ ገዳም ከማኅበረ ገዳሙ አንድነት ገብተው በአርድእትነት፣ አንድ ዓመት፣ ጫጋል አማኑኤል በቅዳሴ አንድ ዓመት በሌላም አገልግሎት ተመድበው ብዙ ፈተናን ታግሶ በማሳለፍ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኩል በፀባቴነት ሥራ እስከተመደቡበት ወቅት ድረስ ደረጃ በደረጃ ቀና መንፈሳዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
+ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የቀድሞው ፀባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው መጽሐፍ ለመማር ፍላጎት ስለነበራቸው በመምህር ገብረ ኢየሱስ ስም በተቋቋመው መንፈሳዊ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ እንዲማሩ ከበላይ አካል ተፈቅዶላቸው በዚሁ ዓመት ከዚህ ትምህርት ቤት ገብተው ከመምህር ብርሃኑ ወልደ ሥላሴና ከመምህር ገብረ ሕይወት ገብረ ኢየሱስ ዘንድ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል መዐርገ ምንኵስናን በዚህ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ ከዚያም መዐርገ ቅስናን በዚሁ ዓመተ ምሕረት ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተቀብለዋል። ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ዘንድ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡
+ ፀባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው ይህን ታላቅ መንፈሳዊ ዓላማ በቸልተኝነት ሳይሆን በቅንነት ተቀብለው የሞግዚትነቱን ሥራ ጭምር ይዘው ምክትል ሆነው በማስተማር፣ ደቀ መዛሙርቱን በማስቀጸል ተግባር ላይ እንዳሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልካም ፈቃድ ሰኔ ፲ ቀን ፲፱፻፺፬ (ሰኔ 10/ 1994) ዓ.ም ለታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ (ፀባቴ) ሆነው ተሾሙ፡፡ በዚሁ ገዳም ተሹመው ይህን ታላቅ ኃላፊነት ከተረከቡ ጀምሮ በገዳሙ ውስጥ ብዙ የልማት ሥራዎች እንዲሠሩና እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡
+ ፀባቴ ተክለ ሐዋርያት ባሳዝነው ባበረከቱት መንፈሳዊ አገልግሎት፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቃታቸው ተመዝኖ ሐምሌ ፱ ቀን ፲፱፻፺፯ (ሐምሌ 9/ 1997) ዓ.ም በተደረገው የጳጳሳት ምርጫ ከሌሎች ዕጩ ቆሞሳት ጋር ተወዳድረው የድምፅ ብልጫ ስላገኙ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል፡፡
ከዚያም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል። ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ ነበር።
➕➕➕➕➕
(ምንጭ:- የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት )