“ደኅና ነኝ፤ ሁላችም በጸሎታችሁ አስቡኝ” (ቅዱስ ፓትርያርኩ)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያሳለፍናቸው በዓላት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቀረቡ።
ቅዱስነታቸው በሸገር ሀገረ ስብከት በኮየ ፈጨ ክፍለ ከተማ በፋንታ መድኃኔዐለም ደብር የከተራ በዓል እለት ሕይወታቸውን ላጡ ኦርቶዶክሳዊያንም ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ለበዐላቱ መሳካት ምስጋናቸውን ፤ አደጋ ለደርሰባቸው ደግሞ ሐዘናቸውን በገልጹበት ጊዜ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ፤ የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፤ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ የተለያዩ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊ አባቶች ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በክብረ በዓላቱ ያልተገኙት ባጋጠማቸው የጤና ችግር ምክንያት መሆኑንም ጠቁመው አሁን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ባሳላፍናቸው ቅዱሳት የቤተክርስቲያንበዓላት በአካል ባይገኙም ሥነ ስርዓቱቶችን ግን ከአባቶች እና ከመገናኛ ብዙሃን መከታተላቸውም አስታውሰዋል፡፡
አያይዘውም “አሁን በሕክምና ላይ ነው ያለሁት ፤ ደህና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ በሃገር ውስጥም በውጭም ያላችሁ ወገኖቼ በእውነቱ በጣም እንዳሰባችሁ እሰማለሁ፤ ስለ ሐሳባችሁ ስለመጨነቃችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ፤ ሁላችሁም በጸሎት አስቡን ’’ብለዋል፡፡
ቅዱስ አባታችን በመጭዎቹ በዓላት ደግሞ ልክ እንደወትሮው ሁሉ አባታዊ ቡራኬ ለመስጠት እግዚአብሔር አምላክ እንደሚያበቃቸው ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውንም በዚሁ ጊዜ አመላክተዋል፡፡
+++++++++++++++++++++++++++++++++++
(ምንጭ:- የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት)