አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ለቀቀች።
አሜሪካ ከዓመት በፊት በሰጠችው ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ከሆነው የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) አባልነት በይፋ ለቅቃ ወጣች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩበት ዕለት ካስተላላፏቸው ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የሆነው ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣት ተግባራዊ ሆኗል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከሚገኘው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት እንዲነሳ ተደርጓል።
ከዚህ በኋላ አገሪቱ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ውስን እና ከተቋሙ መውጣቷን ለማጠናቀቅ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተነግሯል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት የጤና ባለሥልጣን ” በድርጅቱ ውስጥ በታዛቢነት የመሳተፍም ሆነ መልሶ አባል የመሆን ዕቅድ የለንም ” ሲሉ ተናግረዋል።
በበሽታዎች ቁጥጥር እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው በሌሎች የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ ድርጅት በኩል ሳይሆን በቀጥታ ከአገራት ጋር ለመሥራት አቅዳለች።
በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመራው እና ከ190 በላይ አገራትን በአባልነት ከያዘው ተቋም አሜሪካ ለመውጣት መወሰኗ በአሜሪካ እንዲሁም በቀሪው የዓለም ክፍል የሚከናወኑ የጤና ሥራዎችን የሚጎዳ መሆኑ እየተነገረ ነው።