አሜሪካ ዛሬ በይፋ ከአለም ጤና ድርጅት ትወጣለች ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ አመት በፊት ወደ ነጩ ቤተመንግስት ሲመለሱ አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት የሚያስወጣትን መመሪያ መፈረማቸው ይታወሳል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም( ዶ/ር) “የአሜሪካ መውጣት አሜሪካንም ቀሪውን አለምንም ይጎዳል” በማለት አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤነውና እንድትመለስ ሲጠይቁም ነበር።
እስካሁን በሀገሪቱ ህግ መሰረት አሜሪካ ከመውጣቷ በፊት ቀሪ ክፍያዋን መክፈል እንዳለባትና አንድ አመት መቆየት እንዳለባት ስለሚያስገድድ አሜሪካ ሳትወጣ ቆይታለች። ይህ ቀን ዛሬ ያበቃል።
ባለፉት ጊዜያት አሜሪካ 18 በመቶውን የአለም ጤና ድርጅት ፈንድ የምትሸፍን የነበረ ሲሆን፣ ለአለም ጤና ድርጅት በ2024ና በ2025 መክፈል የነበረባትን ከ260 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብም አልከፈለችም ተብሏል።
የስቴት ዲፓርትመንት ቃለ አቀባይ የድርጅቱ ለአሜሪካ መረጃ አለመስጠት አሜሪካን ብዙ ትሪሊየን ዶላር አስወጥቷታል ማለታቸው ተዘግቧል።
ቢል ጌትስን ጨምሮ በርካቶች አሜሪካ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ድርጅቱ ትመለሳለች ብለው እንደማያምኑ ሲገልጹ፣ የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት ስለ አሜሪካ መውጣትና እንዴት እንደሚሆን በመጪው የካቲት ወር እንደሚመክሩም ተነግሯል።