የብሪታንያ ዓቃቤ ሕግ ኢትዮጵያዊውን ስደተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ

የብሪታንያ ዓቃቤ ሕግ፣ የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ በሆነ አንድ ሆቴል ውስጥ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ጾታዊ ትንኮሳ ፈጽሟል በማለት የጠረጠረውን ኢትዮጵያዊውን ስደተኛ መላኩ ገብረሰንበትን ፍርድ ቤት አቀረበ።

የ23 ዓመቱ መላኩ ትናንት በሳውዝአምፕተን ከተማ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲኾን፣ ተከሳሹ ክሱን በማስተባበል ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበል መቅረቱን የብሪታንያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ፖሊስ የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ በሆነው ሀይፊልድ ሀውስ ሆቴል ተከሳሹ የተጠረጠረበትን የጾታ ትንኮሳ ክስተት በመመርመር ላይ ነው ተብሏል። ተከሳሹ የጥገኝነት ጥያቄው እንዲታይለት ለአምስት ዓመታት ሲጠባበቅ እንደቆየ ተገልጧል።