ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የሚድሮክ ኩባንያ ንብረት በኾነው የለገደምቢ ወርቅ ማዕድን ማውጫ አካባቢ ነዋሪዎች ውርጃን ጨምሮ የተለያዩ የጤና እክሎች እየገጠሟቸው መሆኑን እንደገለጡ አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
ድርጅቱ፣ ማዕድን ማውጫው ሜሪኩሪን ጨምሮ የተለያዩ አደገኛ ኬሚካሎችን እንደሚጠቀም ገልጧል።
በቀጣዩ ሳምንት የተመድ ሕጻናት መብት ተከታታይ ኮሚቴ በለገደምቢ ወርቅ ማውጫ አካባቢ የሚገኙ ሕጻናትን መብት ጨምሮ በኢትዮጵያ የሕጻናት መብት ዙሪያ እንደሚወያይ የጠቀሠው ድርጅቱ፣ ከሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በመሆን የማዕድን ማውጫው በደቀነው አደጋ ዙሪያ ለኮሚቴው ስጋቶቹንና ምክረ ሃሳቦችን ማቅረቡን ገልጧል።
ኮሚቴው ሲሰበሰብ፣ መንግሥት ማዕድን ማውጫው ሥራ እንዲያቆም፣ ማዕድን ማውጫው ባስከተለው የአካባቢ ተጽዕኖ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግና ተጎጅ ወገኖች ካሳ፣ የሕክምና ድጋፍና ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲያደርግ እንዲጠይቅ አሳስቧል።