የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንቱን 21 አማካሪዎች ሹመት የሚሽር ውሳኔ አሳለፈ።
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ያቋቋሟቸው የአማካሪ ቢሮዎች እና በነዚህ ቢሮዎች ላይ የተሾሙ 21 ግለሰቦች ሹመት ሕገ-መንግስታዊ መሰረት የሌለው ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን፣ እነዚህ የሥራ መደቦች ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዙም አዝዟል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ መንግስት የህዝብን ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመ አይደለም በሚል በቀረበበት አቤቱታ ላይ ተመስርቶ ነው።
ውሳኔውን ያሳለፉት ዳኛ በሰጡት ብይን፣ የእነዚህ ቢሮዎች አወቃቀር እና የምልመላ ሂደት ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ፣ በሕዝብ አገልግሎት ኮሚሽን (Public Service Commission) በኩል መከናወን ሲገባው ያለአግባብ መቋቋማቸውን ገልጸዋል።
አማካሪዎቹ ለሚያገኙት ከፍተኛ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም የሚወጣው የህዝብ ግብር ሕጋዊ መሰረት የለውምም ተብሏል።
ከፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ ባይኖርም፣ መንግስት በውሳኔው ላይ ይግባኝ ሊጠይቅ እንደሚችል ይጠበቃል።
ዘገባው ዘስታር ኬኒያ እና ዘኬንያ ታይምስ ነው።