” ጂቡቲ ላይ ከ15 ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ህፃናት ጎዳና ላይ አሉ። ጂቡቲ ውስጥ የቀሩ ” – የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
⚫️ “ለፍልሰት ዋናው ምክንያት ድህነት ነው!”
ከሀገር የተደዱ ከ15 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ህፃናት በጂቡቲ ጎዳናዎች እንደሚገኙ፣ በሦስት አመት ከፍልሰት ከተመለሱት 500 ሺሕ ዜጎች 10 ሺሕ የሚሆኑት ህፃናት እንደሆኑ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴዔታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ በም/ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚመራ ምክር ቤት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚኒስቴሩ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ፣ የ14 ዓመት ታዳጊዎች ጭምር ከሀገር እንደሚወጡ በርካታ ህፃናት ጭምር በመንገድ ላይ እንደሚሞቱ፣ ለአሸባሪነት፣ ለውትድርና እንደሚመለመሉ፣ አካላቸው እንደሚሰረቅ ጭምር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
አቶ ደረጀ በዝርዝር ምን አሉ ?
” የኢትዮጵያ ህፃናት ከ14 ዓመት ጀምሮ ከሀገር ይወጣሉ። ለምሳሌ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ በኩል የድሮ ባቡር መስመሮች ሁሉ ሚሰሩበት ሁኔታ አለ፤ በዚያ ላይ ተንጠልጥለው የሚወጡ ህጻናት አሉ። በአፋር፣ በድሬዳዋ የሚወጡ አሉ።
ጂቡቲ ላይ ከ15 ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ህጻናት ጎዳና ላይ አሉ። ጂቡቲ ውስጥ የቀሩ። ድንበር አቋርጠው ከገቡ በኋላ ደግሞ የመን ውስጥ የተያዙ በርካታ ህፃናት አሉ። እነዚህን ለአሸባሪነት፣ ለውትድርና ይመለምሏቸዋል። የሰውነታቸውን አካል ይሰርቋቸዋል።
ህፃናት ሲሆኑ ደግሞ ከፍተኛ ውስብስብ ችግር ውስጥ ያስገቧቸዋል። ለእንደዚህ አይነት ህፃናት ቶሎ መድረስና ማምጣት ስለሚያስፈልግ መንግስት በርካታ ህፃናት መልሷል።
ህፃናቱ እንደተመለሱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት፣ እስከዚያው በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚቆዩ የማድረግ ሥራ ይሰራል። ቤተሰብ ካልተገኘ ለጉዲፊቻ የሚሰጡባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ቤተሰብ ጋር ከተገናኙ ጥሩ አማራጭ ተብሎ ነው የሚታሰበው። ”
ህፃናት ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ገጠመኝ ምን ይሁን ?
” በተግባር ያየናቸው ነገሮች መንግስት አልባ የሆኑ አካባቢዎች አሉ። አንዱ መንግስት አልባ የሆነ አገር የመን ነው።
በጂቡቲ በኩል የመን መዳረሻውን ሳዑዲ አረቢያ አድርገው የሚሄዱ አሉ። የመን ላይ ይያዛሉ፤ ለጦር የሚንቀሳቀሱ ሰዎችም ለውትድርና ይመለምሏቸዋል፤ የማሸበር ሥራ ውስጥ ያስገቧቸዋል።
ህፃናት ላይ የሚደረገው የጉልበት ብዝበዛና ህገወጥ ተግባር ጠንከራ ነው። ሴቶቹም፣ ወንዶቹም Sexually Abuse ይደረጋሉ። ለብዙ ጉዳት የተዳረጉ ህፃናት አሉ። ”
ምን ያህል ፍልሰተኛ ህጻናት ተመለሱ ?
” ከ10 ሺሕ ያላነሱ ፍልሰተኛ ህፃናት በሦስት ዓመት ተመልሰዋል። ከአጠቃላይ 500 ሺሕ ተመላሾች 10ሺሕ ህፃናት ናቸው።
ከእነዚ ህመካከል አንዳንዶቹ እዚያው ሀገር የተወለዱ ናቸው። ጉዞ ላይ እያሉ ተደፍረው፣ እዚያም ሀገር ከገቡ በኋላ በአሰሪዎቻቸው ተደፍረው የወለዷቸው ህጻናት አሉ። ”
የሚሰደዱ ዜጎች ምክንያታቸው ምንድን ነው?
” ለፍልሰት ዋናው ምክንያት ድህነት ነው። ምንም ልንዋሸው የማንችለው ነው። ድህነት በጣም የከፋ ነገር ነው። ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎች ለዚህ ይጋለጣሉ። በሀገራቸው የሚኖሩበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
ሁለተኛው፥ በአብዛኛው ደግሞ ድህነት ባልከፋባቸው ቦታዎች ላይ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ ሕገወጥ ደላሎች እና ሰው አዘዋዋሪዎች አሉ። የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ NGO ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የተሻለ ይከፈላቸው የነበሩ ሰዎች ከፍልሰት ተመላሽ ሆነው አግኝተናቸዋል።
ህፃናት በአቻ ግፊት ነው ከሀገር የሚወጡት፤ ሳያውቁ የሚሄዱም አሉ፤ ወላጆች ሲያሳድጓቸው ጭምር ‘ውጭ ሀገር ሂደህ ታሳልፍልኛለህ’ ብሎ እየነገሩ ስለሆነ ይህ በራሱ ተፅዕኖ ይፈጥራል። በዚህ ሁኔታ ሂደው በውሃ ጥም፣ በጀልባ መገልበጥ፣ በረሃውን ባለመቻል የሚሞቱ በርካታ አሉ። አብዛኛዎቹ በወላጅ ግፊት የሚሄዱ ናቸው። ጉዳቱ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የሰውነት የአካል ክፍል መሰረቅ ጭምር ነው። ”
ለመሆኑ ክፍተቱና መፍትሄው ምንድን ነው ?
” በመንግስት በኩል ህጎች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። ግን ህግ በማውጣት ብቻ ማስቆም አይቻልም። ስለዚህ ማህበረሰቡ መተባበር አለበት፤ ፍልሰተኞችም ከዚህ መታቀብ አለባቸው። ንብረት ሸጠው፣ ተበድረው ልጆቻቸውን ወደሌላ ሀገር ይልካሉ። ልጆቻቸው እዚሁ እንስራ ቢሉ ግን ያንን አያደርጉላቸውም።
በአገር ባለው አማራጭ እንዲያድጉ ማድረግ አለባቸው። ህገወጥ ደላሎችን አጋልጦ መስጠትም ያስፈልጋል። ማህበረሰቡ ነው እየከለላቸው ያለው። የፍትህ አካላትም ህገወጥ ደላሎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ተገቢውን ስራ መስራት መቻል አለባቸው። “