የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ፍሰትን የሚያስቆም ግድብ ገንብታለች በማለት ችግሩን መፍታት እንደሚፈልጉ በድጋሚ ተናገሩ።
ግብጽ በግድቡ ሳቢያ ከወንዙ “በቂ ውሃ” ማግኘት አልቻለችም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ካሁን ቀደም በውሃ ውዝግብ ሳቢያ በኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል ሊቀሰቀስ የነበረ ጦርነት አስቁሜያለሁ በማለትም ትናንት በሠጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዓለም በርዝማኔው ቀዳሚ የኾነውን ናይል “ትንሽ ወንዝ” በማለት የጠሩት ሲሆን፣ ሁልጊዜም ናይል ግብጽ ውስጥ እንዳለ ያስቡ እንደነበር ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ፣ የግድቡን ግንባታ አሜሪካ በገንዘብ ደግፋለች በማለት ካሁን ቀደም የተናገሩትን ንግግርም ማስረጃ ሳይጠቅሱ ደጋግመውታል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ናይል ይህን የተናገሩት፣ በወንዙ የውሃ ክፍፍል ዙሪያ በተፋሰሱ አገራት መካከል ያለውን ውዝግብ ለማሸማገል እንደሚፈልጉ ለግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ደብዳቤ በጻፉ ማግስት ነው።