የቤልጂየም ፍርድ ቤት የፓትሪስ ሉሙምባን የግድያ ክስ ዳግም መመልከት ሊጀምር ነው።
የኮንጎ የነፃነት ምልክት የሆኑት ፓትሪስ ሉሙምባ በፈረንጆቹ 1961 የተገደሉ ሲሆን ግድያቸውን በተመለከተ በፍርድ ቤት የተወሰነ ውሳኔ አልነበረም።
የሉሙምባ ቤተሰቦችም ለአመታት ፍትህ ለማግኘት ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን የቤልጂየም ፍርድ ቤትም በግድያው ከተጠረጠሩት መካከል በህይወት በቀረው ብቸኛ ሰው ላይ የቀረበውን ክስ መስማት ሊጀምር ነው።
ሉሙምባ ከ65 አመታት በፊት ከተገደሉ በኋላ ሰውነታቸው በአሲድ እንዲጠፋ የተደረገ ሲሆን ግድያው በቀድሞ ቅኝ ግዢዋ ቤልጂየም እገዛ እንደተደረገበት ይታመናል።
ግድያው በወቅቱ ሲፈጸም ከነበሩት አመራሮቸ መካከል በህይወት ያለው በወቅቱ የቤልጂየም ዲፕሎማት የነበረው የ93 አመቱ ኤቲን ዳቪግኖን ብቻ ነው።
ግለሰቡ በተደጋጋሚ ቤልጂየም በሉሙምባ ግድያ አልተሳተፈችም ቢልም የቤልጂየም የፌደራል ምርመራ ቢሮ ከሉሙምባ ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ መስርቶበታል።
የነፃነት መሪው ግድያ የብዙዎችን ልብ የሰበረ ሲሆን ፍትህ አለማግኘቱ ደግሞ ብዙዎችንም ያስቆጨ ነበር።
ዘገባው የአፍሪካ ኒውስ ነው።