ቅዱስነታቸው በመንበረ ክብራቸው አሉ። በቅርቡ የመውደቅ አደጋ ገጥሟቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል።

” ቅዱስነታቸው በመንበረ ክብራቸው አሉ። የእድሜን መግፋት ተከትሎ የመጣ መጠነኛ ህመም ገጥሞቸው ነው። የተወሰነ አሁን ለውጥ አላቸው ” – የቤተክርስቲያኗ የሥራ ኃላፊ

🟡 ” በቅርቡ የመውደቅ አደጋ ገጥሟቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል። የመሻል ሁኔታ በማሳየት በዊልቸር እየተደገፉ የተወሰኑ ጊዜያት ራሳቸው መሰብሰብ ችለዋል! “

በተለይ በበዓላት ወቅት በአካል ብቅ በማለት ቃለምህዳንና ቡራኬ የሚሰጡት፣ ለዓለም ጭምር ሚጸልዩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዘንድሮው በዓለ ጥምቀት አልተገኙም።

ይህ ለምን እንደሆነ ቤተክርስቲያኗ ቀድማ በይፋ ያሳወቀችው ነገር የለም። ይህን ተከትሎም፣ ምዕመናን ” አባታችን የት ገቡ? ቡራኬያቸውን እየጠበቅን ነበር ምን ሆነው ነው ? ለምን በግልጽ አይነገረንም ? ” የሚል ጭንቀት አዘል ጥያቄ በስፋት እያቀረቡ ናቸው።

በጉዳዩ የተጨነቁ አንዳንዶቹ ” ብፁዕ አባታችን የጠፉብን በደኀና እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፤ ልዑል እግዚአብሔር ይጠብቅልን ” ሲሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ” ብፁዕነታቸው ከፕትርክናቸው ተነስተዋል፤ ለምን ይህ ሆነ ? ” ብለው እስከመጠየቅ ደርሰዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቃት ቤተክርስቲያኗ ምን አለች ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ብፁዕነታቸው በዘንድሮው ጥምቀት በዓል ተገኝተው ለህዝቡ የተለመደውን ቡራኬ ያልሰጡት ምን ሆነው ነው ? ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲንን የጠየቀ ሲሆን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የቤተክርስቲያኗ የሥራ ኃላፊ፣ ” በበዓሉ ያልተገኙት ወድቀው አደጋ ደርሶባቸው ” መሆኑን ገልጸዋል።

” ቅዱስነታቸው በዘንድሮው ጥምቀት በዓል አልተገኙም። ይህም የጤና ጉዳይን ተከትሎ የመጣ ነው። በሙሉ አቅም ምዕመናንን መባረክ ስለሚጠበቅባቸው ያንን ለማድረግ የሚያስችል የጤና ሁኔታ ላይ አይደለም ያሉት” ሲሉ ” እንደ አንድ የሥራ ኃላፊ በቅርበት የማውቀው ” ያሉትን ነግረውናል።

በዚህም፣ ” ቅዱስነታቸው የገጠማቸው መጠነኛ ህመም ነበር፤ በቂ ህክምና አግኝተው አሁን በጥሩ ደረጃ እንዳሉና ህዝቡን በፀሎታቸው እየባረኩ እንደሆነ ነው የማውቀው ” ነው ያሉት።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ የቅዱስነታቸው ህመማቸው ምንድን ነው ? በትክክል ምንድን ነው የሆኑት ? ይህ የገጠማቸውስ መቼ ነው ? ሲል እኚሁን የቤተክርስቲያኗን የሥራ ኃላፊ ጠይቋቸዋል።

እሳቸውም፣ ” የማደናቀፍ ነገር ገጥሟቸው በዚያው በመንበረ ክብራቸው ላይ፤ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ለዚያም ሲኖዶሱ ተከታትሎ በቂ ህክምና ተደርጎላቸዋል፤ ህክምናውም ተስፋ አለው። ወዲያውኑ ከህክምና ወጥተው ወደ መንበረ ፓትርያርክ ገብተዋል ” ሲሉ መልሰዋል።

” ይህ የገጠማቸው ባለፈው ታህሳስ ወር ነው። በልደትም ወጥተው ባርከው ነው የተመለሱት። የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆርዮስ ናቸው የቅዱስነታቸውን ቃል በንባብ ያሰሙት እንጅ ቡራኬውንም የሰጡት ቅዱስነታቸው ናቸው፤ ከቀን ወደቀን ጤንነታቸው ጥሩ እየሆነ ነው ” ሲሉም አክለዋል።

” በመጪው የካቲት 24 በዓለ ሲመታቸው ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እዛም ላይ እንደሚገኙ ተስፋ እናደርጋለን ” ያሉት የመረጃ ምንጫችን፣ እሳቸው ለዓለም እንደሚጸልዩት ሁሉ ህዝቡም ለጤንነታቸው በፀሎቱ ሊያስባቸው እንደሚገባ፣ ” የቅዱስነታቸው መቆየት ለኢትዮጵያም፣ ለቤተክርስቲያንም ትልቅ ትርጉም ” እንዳለው ገልጸዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ ቅዱስነታቸው በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ያልተገኙት ” የፕትርክና ለውጥ ስላለ ነው ” በሚል የሚናፈስ መረጃ አለ፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ? የሚል ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

አመራሩም፣ ” ይሄ ፈጽሞ ውሸት ነው። ቅዱስነታቸው በመንበረ ክብራቸው ነው ያሉት። ዛሬም ድረስ 6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው ” ብለዋል።

” ቋሚ ሲኖዶስ ሙሉ ሥራውን እያከናወነ ነው። የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆርዮስ በተሟላ ቋሚ ሲኖዶሱን እየሰበሰቡ፣ ከቅዱስነታቸው መመሪያ እየተቀበሉ፣ ቀን በቀን እያገኟቸው፣ ከብፁዕ ጠቅላይ ስራ አስኪያጁና ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋር ቤተክርስቲያኒቷን እየመሩ ነው ያሉት። ይሄ ነው እውነታው ” ነው ያሉት።

” ቅዱስነታቸው በመንበረ ክብራቸው አሉ።  የእድሜን መግፋት ተከትሎ የመጣ መጠነኛ የጤና ህመም ገጥሞቸው ነው። የተወሰነ አሁን ለውጥ አላቸው። ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጤናቸው ተመልሶ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን እንሚባርኩ ሙሉ እምነት አለን ” ነው ያሉት።

የሥራ ኃላፊው አክለው ምን አሉ ?

” ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ 6ኛው ፓትርያርክ የሁላችንም አባት ናቸው። በእድሜያቸውም ትልቅ አባት ናቸው። እድሜን ተከትሎ በዓይን የሚታይ አንድ እውነታ አለ። ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያገለግላል፣ እርጅናም ይመጣል።

ቅዱስነታቸው ብዙውን ጊዜ በፀሎት ነው የሚኖሩት፣ ፍፁም መናኝ አባት ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ወደ መንበረ ፕትርክናም ሲሾሙ እድሜያቸው ገፋ ያለ አረጋዊ አባት ናቸው። ከተሾሙ 10 ዓመት ሆኗቸዋል። የእድሜ መግፋትን ተከትሎ በቅርቡ የመውደቅ አደጋ ገጥሟቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል፤ ጥሩ ለውጥ በመምጣቱም ከሆስፒታል ወጥተው ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰው አገግመው በፀሎት እየታገዙ ነው።

ቋሚ ሲኖዶስም ለተወሰኑ ጊዜያት በተወካይ አማካኝነት ይሰበሰብ ነበር። በኋላም ትንሽ የመሻል ሁኔታ በማሳየት በዊልቸር እየተደገፉም የተወሰኑ ጊዜያት ራሳቸው መሰብሰብ ችለዋል።

የባለፈው በዓለ ልደትን አስመልክቶም በቋሚ ሲኖዶስ አባቶች ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ ቃለ ቃለምህዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል” ሲሉ አስታውሰዋል።

የሥራ ኃላፊው ምን አስተያየት ሰጡ ?

ሚዲያ ከመጠየቁ በፊት የቤተክርስቲያኗ ሚዲያዎች፣ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ክፍል፣ ቋሚ ሲኖዶስም ብፁዕነታቸው ያሉበትን ሁኔታ ማሳወቅ እንደነበረባቸው ገልጸው፣ ” እነዚህ ክፍተቶች አሉ ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

” ህዝቡ ይጠይቃል፤ ምክንያቱም ብፁዕነታቸው የቤተክርስቲያኗ መሪ አባት፤ የመንጋው ጠባቂ ናቸው። ቤተክርስቲያን ሲባል ፓትርያርኩ ናቸው ሊወክሉ የሚችሉት። እናም መደበቅ የለበትም። ድብቅ ሊሆንም አይገባም ” ነው ያሉት።

” ህመም፣ እርጅና ወንጀል አይደለም ” ያሉት እኚሁ ታማኝ የመረጃ ምንጫችን፣ ” ለህዝቡ በቂ መረጃ ሊሰጠው ይገባል። አባታችን የት ሄዱ? ብሎ ሲጠይቅ የማወቅ መብት አለው። አባቴ የት ሄዱ? ብሎ ልጅ መጠየቅም ይችላል። የጤናቸው ጉዳይ ያሳስበዋልና ” ሲሉም አክለዋል።