የወልቃይት-ጠገዴ-ሁመራ ዞን አስተዳደር፣ በወልቃይት፣ ጠገዴ እና ሁመራ አስተዳደራዊ አከላለል ጉዳይ ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት “ወሰን” እና “ዓላማ” ውጭ ነው አለ።
የዞኑ አስተዳደር ስለ ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ሁመራ ታሪካዊ አስተዳደራዊ አከላለልና የማንነት ጥያቄ ዙሪያ አዲስ ባሠራጨው የጽሁፍ ማብራሪያ፣ ፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት የተፈራረሙት “ግጭት ለማቆም” እና “ለተያያዥ ሂደቶች” ብቻ ነው ብሏል።
የዞኑ አስተዳደር፣ የፌደራል ተቋማት ዞኑ በአማራ ክልል መዋቅር ሥር የሚገኝ መኾኑን አውቀው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብሏል። ከጦርነቱ ወዲህ ያለው የአካባቢው አከላለል ከ1983 በፊት ከነበረውም ኾነ አሁን ካለው ፌደራላዊ አወቃቀር ጋር የተጣጣመ ነው ያለው የዞኑ አስተዳደር፣ ይህን እውነታ መገንዘብ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ለሚደረግ ገንቢ ንግግር አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሷል።