አሳዛኝ መረጃ ከዋግኽምራ ሰቆጣ!
የአገዛዙ ወታደሮች ሲሸሹ በየመንደሩ ጥለውት የነበረው የመድፍ ቅንቡላ ፈንድቶ ከአንድ ቤተሰብ የአምስት ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ!
አደጋው የደረሰው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ 03 ቀበሌ ልዩ ስሙ በልታርፍ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ላይ ሲሆን፡ የአገዛዙ ወታደሮች ያለጥንቃቄ ጥለውት የነበረውን የመድፍ ቅንቡላ አንድ የአከባቢው ሰው አንስቶ ወደቤቱ በማስገባት ለመቀመጫ አገልግሎት ለማዋል ሲሞክር ፈንድቶበታል።
በዚህም ከአንድ ቤተሰብ ብቻ ህፃናትና ታዳጊዎችን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን የአከባቢው ነዋሪዎች ለመረብ ሚዲያ ተናግረዋል።
አደጋው የደረሰው ጥር 07/2018 ዓ/ም ሲሆን፡ ሕይወታቸው ካለፈው አምስት ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት መረብ ሚዲያ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች።
በተጨማሪም የቤት እንስሳት ተገድለዋል፡ መኖሪያ ቤቱም ወድሟል።
በአማራ ክልል የተሰማሩት የአገዛዙ ወታደሮች ተቀጣጣይ ፈንጆችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ሆን ብለው ጭምር ህፃናት በሚበዙበት አከባቢዎች ጥለው ይሄዳሉ።
ህፃናቱም መጫወቻ መስሏቸው ያነሱትና እጃቸው ላይ ፈንድቶ ሕይወታቸውንና አካላቸውን ይቀጥፋል።
ህፃናት ብቻ ሳይሆኑ ነፍስ አዋቂዎችም ጭምር ከግንዛቤ እጥረት ወድቆ የሚያገኙትን መሣሪያ “ማረሻና ቢለዋ” ለማሰራት በሚል በሚያነሱበት ወቅት እጃቸው ላይ ፈንድቶ ሕይወትን እስከማሳጣትና ንብረትን እስከማውደም የደረሰ የከፋ ጉዳት ሲያደርስባቸው ይስተዋላል።
በየትኛውም የክልሉ አከባቢዎች የአገዛዙ ወታደሮች ሆን ብለው ጭምር የሚጥሉት የጦር መሣሪያ ተተኳሽ ወይንም ተቀጣጣይ ፈንጅ ወድቆ ሲገኝ በአቅራቢያው ለሚገኙ የፋኖ ኃይሎች ጥቆማ በመስጠት፡ የፋኖ ፈንጅ አምካኞች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲያስወግዱት ማስደረግ እንዲቻል ይህንን መረጃ የምትመለከቱ ሁሉ መረጃውን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የበኩላችሁን እንድትወጡ መረብ ሚዲያ ጥሪ ያቀርባል።