ኤርትራ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት ለመጀመር “ሰበብ እየፈለገ ነው” አለች

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኤርትራ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቃሱ ታጣቂዎች የተላኩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥይቶችን ያዝኩ ማለቱን ተከትሎ ኤርትራ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት “ጦርነት ለመጀመር ሰበብ እየፈለገ ነው” አለች።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ለኢትዮጵያ ውንጀላ ለሮይተርስ የዜና ወኪል የብልጽግና መንግሥት በኤርትራ ላይ ጦርነት ለመጀመር ሰበብ እየፈለገ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“የብልጽግና መንግሥት ለሁለት ዓመታት ያህል ጦርነት ለመጀመር ሲያደርግ ለነበረው መቁነጥነጥ ሐሰተኛ ባንዲራውን እያውለበለበ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ መንግሥት በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያ ጥይቶችን እየሰጠ ነው በማለት ወንጅሏል።

ፌዴራል ፖሊስ ጥር 6/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል።

የኤርትራ መንግሥት ግን ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት ውንጀላ ጦርነት ለመጀመር የቀረበ የሐሰት ውንጀላ ነው ሲል አጣጥሏል።

የፌደራል ፖሊስ ውንጀላን ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ጥቃት ለመክፈት ሰበብ እየፈለገች ነው ብለዋል።

ፌዴራል ፖሊስ፤ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የጦር መሣሪያዎች የኤርትራ መንግሥት “ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር” በትግራዩ ህወሓት በኩል የተላኩ ናቸው በማለት ከስሷል

ተያዙ የተባሉት ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ሲሆኑ፣ ሲያጓጉዟቸው የነበሩ “ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ” ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አመልክቷል።

ፖሊስ “በስውር የተላኩ” ያላቸው 41,999 የክላሽ ጥይት፣ 14,000 የብሬን ጥይት እና 800 የድሽቃ ጥይት በአጠቃላይ 56,799 ጥይቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፖሊስ መግለጫ እንደሚለው ተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገው ምርመራ የጦር መሣሪያ ጥይቶቹ ከኤርትራ መንግሥት የተላኩ መሆናቸውን እና ህወሓት መቀሌ ላይ ተቀብሎ ወደ አማራ ክልል በማስገባት ለፋኖ ለማድረስ ሲንቀሳቀስ ነበር።

ጥይቶቹን ሲያጓጉዙ ተይዘዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ አደረግኩ ባለው ምርመራ “ጥይቶቹ በሻዕቢያ መንግሥት እንደተላኩ እና ጽንፈኛው ህወሓት…ከመቀለ ወደ አማራ ክልል ሸዋ ሮቢት” ለማድረስ መንገድ ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል ብሏል።

ህወሓት በበኩሉ፤ በኤርትራ መንግሥት ተልኳል የተባለውን የጦር መሣሪያ “ጽንፈኛው ህወሓት ከትግራይ…ወደ አማራ ክልል” ለማስገባት ተንቀሳቅሷል የሚል የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጓል። የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም፤ “ጭብጥ የሌለው ውሸት ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።

ህወሓት “ወደዚህ የወረደ ሥራ የሚገባ ፓርቲ አይደለም” ሲሉ የተከላከሉት ቃል አቀባዩ፤ “በውስጣቸው የተፈጠረውን አጀንዳ ለማስቀየስ ሆነ ተብሎ የተሠራ የውሸት ዜና ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ሚካኤል ይህ ዓይነቱ ክስ “የተለመደ ነው” ብለዋል። “ወደ ግጭት እንዳይኬድ እኛ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው። የእነሱ አካሄድ ግን፤ ይመስለኛል ወደዚያ የሚመራ ነገር ነው” ሲሉም የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ወንጅለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር እየተባበረ ነው የሚል ወቀሳ ሲያሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ከአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የብልጽግና መንግሥት በራሱ አገር ሕዝቦች ላይ ጦርነት አውጇል ብለው ነበር።

በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ኤርትራ ጦርነት እንደማትፈልግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ነገር ግን “አገራችንን እንዴት መከላከል እንዳለበን እናውቃለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከዚህ በፊት በድንበር ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ለሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ውጊያ አካሂደው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም በመውረዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥቱ ነህወሃት ጋር የገባውን ጦርነት ተከትሎ በጋራ የዘመቱት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በመካከላቸው መቃቃር ተፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር ማግኘት የኅልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውንም ተከትሎ የአገራቱ ግንኙነት እየተካረረ መጥቷል።

ኤርትራ በአውሮፓውያኑ 1991 ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ ሀገር ሆና ቆይታለች።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሰኞ ከአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የብልጽግና የቀይ ባሕር ፍላጎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ኢሳያስ ለጦርነት ዝግጅት ወደ ኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ሌሎችም የጦር መሣሪያዎች እየገቡ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ፌዴራል ፖሊስ እንደሚለው የኤርትራ መንግሥት የፋኖ ታጣቂዎችን ለማስታጠቅ የሞከረው ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር ነው።