ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ሕገወጥ ገቢና ወጪ እቃዎችን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጡ አካላት ወሮታ መክፈል የሚያስችለውን “ሕገወጥ ዕቃዎችን የሚመለከት መረጃ አሰጣጥ፣ አመዘጋገብ፣ አያያዝና የወሮታ ክፍያን ለመወሰን” በሚል ርዕስ አዲስ መመሪያ ማዘጋጀቱን ዋዜማ ተረድታለች።
የኮንትሮባንድ፣ የንግድ ማጭበርበር፣ የከበሩ ማዕድናትና የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከታቸውና መወሳሰባቸው በመንግሥት ገቢ ላይ አደጋ ማስከተሉ፣ ለመመሪያው መውጣት መነሻ መኾኑን ሚንስቴሩ ጠቅሷል።
በጠቋሚ መረጃ የተያዘ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተወርሶ በሚሸጥበት ጊዜ፣ ለጠቋሚ 25 በመቶና ለዕቃው ያዥ ሕግ አስከባሪ አካላት 20 በመቶ እንደሚከፈል መመሪያው ያዛል።
ሕገወጡን ዕቃ የያዙት ሚሊሺያዎች ወይም ብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኾነ 10 በመቶ የወሮታ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው በመመሪያው ላይ ተደንግጓል።