በአውሮፓ የታገዱ ኬሚካሎች በምስራቅ አፍሪካ ስጋት ሆነዋል።

በአውሮፓ የታገዱ ኬሚካሎች በምስራቅ አፍሪካ ስጋት ሆነዋል።

በአውሮፓ ህብረት ለጤና አደገኛ ተብለው የታገዱ ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች፣ በአውሮፓ ኩባንያዎች ተመርተው ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በስፋት እየገቡ መሆኑን ዴይሊ ኔሽን ዘገባ አስነብቧል።

እንደ ኡጋንዳ ባሉ ሀገራት ከሚገቡት ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት በላኪ ሀገራቸው የታገዱ ሲሆኑ፣ በታንዛኒያ እና ኬንያም በኩባንያዎች ግፊትና በድንበር ላይ በሚደረግ ህገ-ወጥ ዝውውር ምክንያት ቁጥጥሩ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም ነው የተባለው።

እንደ Paraquat ያሉ እጅግ አደገኛ ኬሚካሎች በብሪታንያ ከ2007 ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ቢታገዱም፣ አምራች ኩባንያዎቹ አሁንም ወደ አፍሪካ በመላክ ላይ ናቸው።

በቅርቡ በኬንያ ሜሩ አካባቢ በተደረገ ጥናት፣ በፈተናው ከተሳተፉ ገበሬዎች መካከል 100 በመቶ የሚሆኑት በደማቸው ውስጥ የዚህ አደገኛ ኬሚካል ቅሪት ተገኝቶባቸዋል።

በኡጋንዳ በሀገሪቱ ከሚመዘገቡት ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት በላኪ ሀገራቸው (አውሮፓ) የታገዱ ናቸው። በሌሎችም የቀጠናው ሀገራት በድንበር አካባቢ በህገወጥ መልኩ በሚገቡ መድኃኒቶች ተፈትነዋል።

ዘገባው እንደሚያሳየው ገበሬዎች እነዚህን መርዛማ ኬሚካሎች ያለ ምንም መከላከያ ልብስ እና ጭንብል በእጃቸው ይበጠብጣሉ። ይህም ለከፋ የሳምባ ጉዳት፣ ለቆዳ በሽታ እና ለፓርኪንሰን (የመንቀጥቀጥ) በሽታ ተጋላጭ ይዳርጋቸዋል።

በተጨማሪም አውሮፓ እነዚህን አደገኛ ኬሚካሎች ወደ አፍሪካ ብትልክም፣ በነዚሁ ኬሚካሎች የታከሙ የአፍሪካ የግብርና ምርቶች ግን “ደረጃቸውን ያልጠበቁ” ተብለው ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይገቡ ይታገዳሉ።

በኢትዮጵያም Paraquat እና Endosulfan ያሉ በአውሮፓ የታገዱ ኬሚካሎች አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ መረጃዎች አሉ።

በተለይ አርሶአደሮች ኬሚካሎቹን ያለ መከላከያ ልብስ መርጨታቸውንና ባዶ የኬሚካል መያዣዎችን ውሃ ለመቅዳትና ለቤት ውስጥ አገልግሎት መጠቀማቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።