የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በዓል በኢትዮጵያውን እይታ በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በዓል በኢትዮጵያውን እይታ

ቀሲስ አስተርአየ በጻፏቸው ጦማሮች ሁሉ ከቤተ ክርስቲያናችን ነገረ መለኮትና ቀኖና ተነስተው የሀገርን፣የቤተ ክርስቲያንና የህዝብን ሁኔታ ሳያሳዩ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህም ተጠልተውበታል፣ተብጠልጥለውበታል እንዲሁም ተገፍተውበታል።

በዓለት በሕዝብ ላይ በሚሽከረከሩት ዓመታት ላይ እየታዘሉና እየተደራረቡ የሚከሰቱትን ሀዘንም ደስታም እየደረቡና እያዘሉ የሚመጡ ክስተቶች ናቸው፡፡ ከግሼ የምትመነጨው ዐባይ ወንዝ ጎጃምን ዞራ ጣና እስክተደርስ ከመላ ኢትዮጵያ የሚፈሱትን ወንዞች እያስገበረች እንደምትጓዘው ዓይነት ማለት ነው፡፡

በዓላትም ባንድ ወቅት ባንድ ትልውድ ይጀመራሉ፡፡ በየዓመቱ ሲቀጥሉ በየዘመኑ በቀጣዩ ትውልድ ላይ የተከሰቱትን እየደረቡ ይቀጥላሉ፡፡ ከበዓላቱ አንዱ ጥምቀት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል መነሻው ክርስቶስ “ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” (ማቴ 3፡15 ) ብሎ ሲጠመቅ የተናገረው ቃል ነው፡፡ ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳዊያን ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም (ማቴ 5፡20) ብሎ እንደተናገረው ክርስቲያን በጽድቅ ከሁሉም በልጦ መገኘትን የሚያውጅ ነው፡፡

መጽሐ ካልዕ 6፡4 ላይ ያለውን ጠቅስው አስተምረውናል፡፡ የኤልያስ ተማሪዎች መኖሪያ ቤት ለመስራት ለቤት ግርግዳና ማገር ፍለጋ ጫካ ሄደው ሲቆርጡ ከተማሪዎቹ አንዱ ከሰው የተዋሰው ምሳር (መጥረቢያ) ከእጀታው ተፈንጥሮ ዮርዳኖስ ባሕር ውስጥ ገባበት ፡፡ የፈለገውን እንጨት ሊያገኝ ቀርቶ የተዋሰውን ምሳር አጣ፡፡ ራሱን ይዞ ጮኸ ፡፡ ነቢዩ ምሳሩ በሰጠመበት በኩል ወደ ባሕሩ የእንጨት ቅርፊት ጣለ፡፡ ምሳሩ ተንሳፈፈ፡፡ ቅርፍቱ ሰጠመ፡፡ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ተዓምር ተፈጸመ።

በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንድምታና ትርጓሜ ክርስቶስ በተዋህዶ ሰውን ከሰጠመበት ባህረ ኃጢአት አንሳፎ ለማውጣት በሰው ባህርይ ሰምጦ ገባ፡፡ ሰውን አጸድቀ ማለትም ከሁሉ በላይ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህ ጽድቅ ሽንገላን ሐሰትን የምንዋጋበት ትጥቃችን ሆነ (ኤፌ 6፡10_13)፡፡ “ለእግዚአብሔር እየተገዛን ዲያብሎስን የምንቃወምበት መሳሪያችን ነው (ያዕ 4፡7) ፡፡ አትናቴዎስ የተባለው ክርስቶስ ቦአ ውስተ መርገም በእንቲአነ እንዘ ኢይቀርቦ መርገም አላ ሰምረ ከመ ይጹር መርገመ ዚአነ ወበእንተ ዝንቱ ተብህለ ከመ ውእቱ ቦአ ውስተ መርገም(ሃ ም ፴፡፬)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከዓለም ልዩ ያደረጋት ነገረ መለኮቱን በሰምና ወርቅ መጠቀሟ ነው፡፡ ሰሙ ለሰብአዊ ምድራዊ ክብርና ነጻነት መፋለም ነው። ወርቁ ከረቀቀ ሕሊናችን ጀምሮ በግልም በቡድንም ዘላለማዊ ጥፋት የሚያስከትልብን የዲያብሎስን ክፉ ነገር መዋጋት ነው፡፡ ይህ አባባል ከምሳሩ መንሳፈፍ ከቅርፊቱ መስጠም ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ቅርፊቱ ሰጥሞ በእንጻቱም ምሳሩ መንሳፈፉ ዋናው እንድምታ ክርስቶስ በሰው ባህርይ ገብቶ ግርፋት፣ ስቅላትና ሞት የማይገባው አምላክ የሁሉ ፈጣሪና ሰሪ የኛን የሰዎችን ግርፋት፣ ስቅላትና ሞት መቀበሉን ያስተምረናል፡፡ የቅርፊቱ መንሳፈፍ ዋናው መልዕክት ሰዎች በሰራነው ኃጢአት ምክንያት ግርፋት፣ ስቅላትና ሞት  የሚገባን እያለን ፈጣሪያችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለበደሉና አለሀጢአቱ የኛን በደልና ቀንበሩ መሸከሙና ለእኛ ቤዛ መሆኑንና እኛ ምንም ዋጋ ሳንከፍል ክርስቶስ ዋጋ ከፍሎ በደሙ እንደገዛንና ነጻ እንዳወጣን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ታላቅ መልዕክት ነው።

በጥምቀት በዓል አባቶቻችን በህገ አራዊት ላሉት የሚያስተላስፉት መልዕክት ሰው መግደላቸውንና ፈቃደ ሥጋቸውን መፈጸማቸውን አቁመው “ብትገድል ትገደላለህ “ወደምትለው ኦሪት እንዲመጣ አደረገው፡፡ የሰው አገር ለሚወሩት ክርስቲያኖችም ላንተ ሊደረግብህ የማትፈቅደውን በሌላ ሰው አታድርግ ወደሚለው ወደ ጽድቅ እንዲመጣ ለሁሉም እንደየጠባዩ መልእክት ስታስተላልፈበት ኖራለች፡፡ የጥምቀት በዓል ስናከብር እንዲህ ነበር ብለን የየበዓሉን ዘርፍ ለማሳየት ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ያወጃትን የሕግ ሁሉ ፍጻሜ የሆነችውን ጽድቅን ምሥጢር በቃልም በተግባርም ለመግለጽ ነው።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች ፋኖዎች በህዝብና በአገር ላይ የሚደርሰውን መከራ እየተቀበሉ ኢትዮጵያን ማሻገራቸው ይህን ምሳሌ በመጠቀም ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በሁሉ ነገር ሰባዊ ልዕልናን የሚያንጸባርቅም ነው፡፡ አሁን እንደዚያ ነው ወይ? በዘመኑ ቄሶች የሚሸበሸበው ሽብሻቦ፤ የሚቀርበው ቅኔ ከህዝብ የሚተላለፈው ዝማሬ ምንድነው? ይህን የሚያንጸባርቅ ነው ወይ? ወይስ የዘመኑን ፖለቲካ ገበና መሸፈኛ የበለስ ቅጠል ነውን? የጠመጠሙ አሸብሻቢዎችና ደፍተሮች ገብቷቸዋል ወይ? ሀቁንስ ይዘዋል ወይ? ይህን በተመለከተ ከዛሬ 12  ዓመታት በፊት ቀሲስ አስተርአየ ያቀረቡትን ጦማር በድጋሚ አቀረብንላችሁ። “ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” የሚለውን በአዕምሯችን ይዘን የጥምቀቱን በዓል እናክብር። ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። የጥምቀት በዓል በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ