‘አንድ ቤተሰብ ነው’ የሚባለው ሲዳማ ክልል ላይ አዲስ የተመሰረተው ፓርቲ ተቃውሞ ተነሳበት

” የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አለሙ ጨእቾ ናቸው፣ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር ባለቤታቸው ናቸው። እኔ ፀሐፊ ነበርኩ ሊቀመንበሩ የአጎቱን ልጅ በኔ ቦታ መርጦታል ” – አቶ ሁሴን ቃሲም

➡️ ” ‘አንድ ቤተሰብ ነው’ የሚባለው በእርግጥ ምክትሏ ባለቤቴ ነች፤ በህዝብ ነው የተመረጠችው። ፀሐፊው የወንድሜ ልጅም አይደለም በዝምድና አንገናኝም ” – የፓርቲው ሊቀመንበር

ሲዳማ ክልል ላይ አዲስ የተመሰረተው “ሲዳማ ራሽናል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” (Sidama Rational Party) ከመስራቾቹ በኩል ከወዲሁ ተቃውሞ ተነሳበት።

በመጀመሪያ ” ጠቅላላ ጉባዔ ፀሐፊ አድርጎ ነበር የመረጠኝ ” ሲሉ የሚያስታውሱት አቶ ሁሴን ቃሲም፣ ” ምርጫው ፍትሃዊ አይደለም፤ ከአንድ ቤተሰብ የተሰባሰቡ ናቸው ብዬ ባልኩት ዳግም እንዲካሄድ ከተባለ በኋላ እኔን ከውስጥ አስወጡኝ ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አቶ ሁሴን፣ ” ህዝብ ይፈልገኛል፤ እነርሱ ግን በውስን ሰዎች ከስልጣን አግልለውኛል ” ሲሉም ፓርቲውን ከወዲሁ ተጠያቂ አድርገውታል።

” በመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠራ ከምርጫ ቦርድ 5 ሰዎች ከአዲስ አበባ ተልከው ነበር፤ በዚያ መረጡንና እንደገና መጨረሻ ላይ ማታ ግርግር ነበር ” ብለው፣ የስልጣን ስብጥር ላይ ችግር መኖሩን አስረድተዋል።

” የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አለሙ ጨእቾ ናቸው፣ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር ባለቤታቸው ናቸው። እኔ ፀሐፊ ነበርኩ ሊቀመንበሩ የአጎቱን ልጅ በኔ ቦታ መርጦታል ” ሲሉም አክለዋል።

” ሌላ አንድ ገንዘብ ያዥ የተደረገ ልጅ አለ፤ ብዙ ምዝበራ አካሂዷል። ከአውሮፓ መንግስት የተሰጠንን ኮምፑዩተር እና ፕሪንተር ሁሉ ሸጦ በልቶታል። ከእሱም  ስንከራከር ስለነበር ‘ካልወጣ’ ብሎ ነው ተፅዕኖ ያደረገብኝ ” ነው ያሉት።

” ሊቀመንበሩ አሉታዊ ተፅዕኖ አድርጎብናል ” የሚል ቅሬታ ያነሱት አቶ ሁሴን፣ የፓርቲው አመራሮች ” ከአንድ ወገን የተሰባሰቡ ናቸው ” ሲሉ ገልጸው፣ ግን ፓርቲው ትክክለኛ ጥያቄና ዓላማ ይዞ እንደተነሳ ተናግረዋል።

” በስልጣን ላይ ያሉት የፓርቲው ሰዎች ከአንድ ቤተሰብ ናቸው ” ብለው፣ ” ሌላ ሰው እንዳይገባ አድርገው ያልሆነ ምክንያት እያቀረቡ ያጉላላሉ ” ሲሉ ጠቅሰው፣ ” እኔ ብቻ ሳልሆን በመጀመሪያ ምክትል ሊቀመንበር ተደርገው የተሾመ ነበር፤ አሁን እሱንም እኔንም አገለሉን ” ብለዋል።

” የሊቀመንበሩና ፀሐፊውን ጀርባ ስናጠና የጥቅም ትስስር አላቸው ” ሲሉ የተቹት አቶ ሁሴን፣ ” መጀመሪያ 33ቱም ሰዎች እያንዳንዳቸው 500 ብር አዋጡ ተብሎ ” እንደነበር አስታውሰው፣ “በቃለ ጉባዔም ተነጋግረን መወሰን አለብን ያልወሰነውን ለምንድን ነው አዋጡ የሚባለው ? ” ብለው ሲጠይቁ፣ አለመግባባት መፈጠሩን አስረድተዋል።

” ፓርቲው ለግለሰብ፣ ለግል ጥቅም ተብሎ የተደራጀ አይደለም። የህዝብ ፍላጎት ሌላ ነው፤ መልካም አስተዳደር ይፈልጋል፤ ዘረኝነትን አይፈልግም። መጀመሪያ የተነሳንበት አላማ አሁን የሚስተዋለው አልነበረም፤ መጨረሻው በተወሰኑ ግለሰቦች ነው ችግሩ የተፈጠረው ” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ ፓርቲው ከወዲሁ “ትችት” እና “የአግላይነት” ቅሬታ እየተነሳበት ነው፤ አላማውን እንዴት ማሳካት ይችላል? የፓርቲው አመራሮች “የአንድ ቤተሰብ አባል ናቸው”፣ ፀሐፊው የእርስዎ የአጎት ልጅ”፣ የፓርቲው ም/ሊቀመንበርም “የእርስዎ ባለቤት” ናቸው ተብሏል? ምላሽዎ ምንድን ነው? ሲል የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አለሙ ጨእቾን ጠይቋል።

ምን መለሱ ?

” መጀመሪያ በሸንጎ ቀርቦ ነው ይህ ሁሉ የተደረገው። ከመነሻው ጀምሮ ለዚህ ፓርቲ ያለውን በደል ለማስተካከል እኛ እየታገልን አቶ ሁሴን ቃሲም ከጊዜ በኋላ መጥቶ መጀመሪያ ስንካሰስ ከዚያ በኋላ የራሱን ስራ ለመስራት ወደቤቱ የገባ ነው።

ህዝብ አልመረጠውም። ህዝብ ካልመረጠው አላስቀምጠውም። ህዝብ ‘ጨቅጫቃ ነው፤ የሚመች ሰው አይደለም’ በሚል እጅ አጥቷል። ቅሬታ ካለው አቅርብ ተብሏል ከዚህ በፊት፤ አላቀረበም ” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ሊቀመንበሩን፣ አቶ ሁሴን ቃሲም ግን “ህዝብ መርጦኛል” ነው ያሉት ሲላቸውም፣ “ህዝብ እንዳልመረጠው ህዝብ ዳግም ይሰባሰብና ይበል፤ የሱን ጉዳይ። እንዳውም አጭበርባሪ በመሆኑ የመጡትን ሰዎች ረብሾ ብዙ ሁከት ነው ያነሳው” ሲሉ ከሰዋል።

አቶ አለሙ፣ ስልጣን የያዙ የፓርቲው አመራሮችን በተመለከተ ለተነሳው ቅሬታ ደግሞ፣ “‘አንድ ቤተሰብ ነው’ የሚባለው በእርግጥ ምክትሏ ባለቤቴ ነች፤ በህዝብ ነው የተመረጠችው። ፀሐፊው የወንድሜ ልጅም አይደለም በዝምድና አንገናኝም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል፣ የፓርቲው ሎጎ ላይ ያለው የበግ ምልክት ምንን የሚያመላክት ነው? ስንል ላቀረብነው ተጨማሪ ጥያቄ ደግሞ፣ “የበጉ ምልክት ሰላም፤ ነጻነት ነው። ህዝብን ያገናኛል፤ ሰው አይገፋም፣ አይጎዳም ብለን ነው ምስጢሩን ያስቀመጥነው” ሲሉ መልሰዋል።