” በኋላ ለሚወሰደው እርምጃ እራሱና እራሱ ብቻ ኃላፊነቱን ይወስዳል ” – የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን
የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን ለአድማ ብተና እና ለክልሉ ፖሊስ አባላት በሙሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላለፈ።
ኮሚሽኑ በቅርቡ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሁሉም የአድማ ብተና እና የመደበኛ ፖሊስ አባላት የጦር መሳሪያ እንዲፈቱ ከክልሉ ኮማንድ ፖስት አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሷል።
በዚህም መሰረት ከጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ፈርመው ያወጡትን የጦር መሣሪያ ገቢ ያላደረጉ የአድማ ብተና እና የመደበኛ ፖሊስ አባላት እስከ ነገ ጥር 7 ቀን 2018 ዓ/ም 11:00 ሰዓት ድረስ ገቢ እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል።
” ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ የጦር መሣሪያ በእጁ የተገኘ እንደ ፀረ-ሠላም ተቆጥሮ መንግሥት እርምጃ ይወስድበታል፤ ለዚህም እራሱ እና እራሱ ብቻ ኃላፊነቱን ይወስዳል ” ሲል አስጠንቅቋል።
በጋምቤላ ክልል ሁሉም አድማ ብተናና መደበኛ ፖሊስ አባላት ለምን ትጥቅ ይፈታሉ ? ትጥቅ ያስረክባሉ ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል እስከ ነገ 11:00 ሰዓት ድረስ የአድማ ብተናና መደበኛ ፖሊስ አባላት ትጥቅ ፈተው እንዲያስረክቡ ስለተላለፈው አስቸኳይ ጥብቅ መመሪያ አዲሱን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አነጋግሯቸዋል።
በቅርብ ወደ ኃላፊነት የመጡት ኮሚሽነር ኡማን ኡጉሉ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለፀጥታ መዋቅሩ የተሃድሶ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በክልሉ በ3 ዞኖች ስር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ኢታንግ ልዩ ወረዳ የሚገኙ የአድማ ብተናና መደበኛ ፖሊስ አባላት ትጥቃቸዉን ግምጃ ቤት በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ስልጠና እንዲገቡ መመሪያ መተላለፉን ገልፀዋል።
የቆይታ ጊዜያቸውን፣ የስልጠናውን ቦታና ሁኔታ እንዲሁም ፖሊሳዊ አገልግሎት በማን ይከናወናል ?ለምን ስልጠናዉ በዙር አልተከፋፈለም ? በሚል ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለተነሳላቸዉ ጥያቄ አዲሱ ኮሚሽነር ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የፖሊስ አመራርና አባላትስ ምን አሉ ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ መዋቅሮች የሚገኙ የፖሊስ አባላትና አመራሮችን አነጋግሯል።
” በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የተሃድሶ ስልጠና መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን ” ያሉ ሲሆን ቅሬታ አሳድሮብናል ያሉትን ጉዳይ ተናግረዋል።
ይኸውም ” ስልጠናዉ በዙር አለመደረጉ በፖሊሳዊ አገልግሎቶች ላይ ክፍተት እንደሚፈጥር ፤ በሌላ መልኩ የመመሪያው አስቸኳይነት፣ በህመምና ወሊድ ምክንያት እረፍት ላይ ያሉ ጭምር እንዲገቡ አስገዳጅ መመሪያ መሰጠቱ ” ቅሬታ ፈጠረብን ብለዋል።
” የፖሊስ አዛዥነት የስራ ኃላፊነት ‘ ለሚሊሻ አስረክብ ‘ ተብያለሁ ” ያሉ አንድ የፖሊስ አመራር ” ለክልሉ ሰላምና መረጋጋት የሚከፈል የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ስለሆንኩ በምመራው ወረዳ የሚገኙ የፖሊስ አባላት በአንድ ቀን ትጥቅ እንዲያስረክቡ አድርገናል ” ብለዋል።