አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ75 ሃገራት የቪዛ ሂደቶችን ልታቋርጥ ነው።
የአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት የውጪ ሃገር ዜጎች ዳይቨርሲቲ ቪዛ (DV)ን ጨምሮ ወደ አሜሪካ ሄደው በቋሚነት መኖር ሲፈልጉ የሚሰጣቸው ቪዛ (Immigrant Visa) ሂደት በ75 ሃገራት እንደሚቋረጥ ተገልጿል።
ፎክስ ኒውስ የስቴት ዲፓርትመንትን የውስጥ ማስታወሻ ተመለከትኩ ብሎ ባወጣው መረጃ፣ እርምጃው ከፊታችን የፈረንጆቹ ጥር 21፣ 2026 ጀምሮ ወደ ስራ ይገባል።
ይህ ውሳኔ በርካታ የዲቪ አሸናፊዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል። የዲቪ አሸናፊዎች በዚህ ውሳኔ ምክንያት ቪዛ የማግኘት እድላቸው ችግር ውስጥ ይገባል።
ሂደቱ ይቋረጥባቸዋል ከተባሉ ሃገራት መካከል ፦
– ኢትዮጵያ
– ግብፅ
– ሶማሊያ
– ኤርትራ
– ሩሲያ
– ሱዳን
– ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል።
የስቴት ዲፓርትመንት ውሳኔ በመንግስት ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሚሆኑ የውጪ ሃገር ሰዎችን ለመቀነስ ነው ተብሏል።
ባለፈው ህዳር የቪዛ ኦፊሰሮች የአመልካቾችን ፦
° ጤና፣
° የቋንቋ ክህሎት፣
° ፋይናንስና የተለያዩ መመዘኛዎችን በመመልከት በመንግስት ድጋፍ ለመኖር የሚፈልጉ አይነት ከሆነ ቪዛ እንዲከለክሏቸው ታዘው ነበር።
የስቴት ዲፓርትመንት ቃለ አቀባይ ቶሚ ፒጎት የ75ቱ ሃገራት የቪዛ ሂደት ስቴት ዲፓርትመንት የመንግስትን ድጋፍ የሚጠቀሙ የውጪ ዜጎች እንዳይገቡ ለመከላከል እንዲቻል የቪዛ ሂደቱ እስኪገመገም እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካ መንግስት ድጋፍ በመቀበል የሚኖሩ የውጪ ሃገር ሰዎችን ቁጥር ይፋ አድርገው ነበር።
ትራምፕ በአሜሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጅ ስደተኞች መካከል 47.6% ያህሉ ቢያንስ ከቤተሰብ አንዱ የመንግስት ድጋፍ ተጠቃሚ እንደሆኑ (https://t.me/tikvahethmagazine/26859) ገልጸዋል።
የቪዛ ሂደቱ በስቴት ዲፓርትመንት እስኪገለጽ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ይቆያልም ተብሏል።
በሌላ በኩል ጊዜያዊ ቪዛ ማለትም ፦
– የቱሪስት /የጉብኝት/ ቪዛ
– የተማሪዎች የትምህርት ቪዛ
– አብዛኛው የስራ (ቢዝነስ) ቪዛ የአሁኑ ውሳኔ እንደማይመለከታቸው ተነግሯል።