የአሜሪካ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት፣ የአሜሪካውን የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት እድል (አጎዋ) ለሦስት ዓመታት አራዘመ። ምክር ቤቱ የአጎዋን የቆይታ ጊዜ ያራዘመው፣ ከእድሉ ተጠቃሚ የአፍሪካ አገራት ምርቶችን የሚገዙ የአሜሪካ ኩባንያዎች ገበያቸው እንዳይዛባ እና በአጎዋ ስምምነት ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ማሻሻያ እስኪደርግበት ድረስ መኾኑን ገልጧል። የአጎዋ የጊዜ ቆይታ የተጠናቀቀው ባለፈው መስከረም ሲኾን፣ በድጋሚ ላይታደስ ይችላል የሚል ስጋት ሠፍኖ ቆይቶ ነበር።
ምክር ቤቱ፣ የአጎዋ የጊዜ ቆይታ መራዘሙ፣ ቻይና እና ሩሲያ አፍሪካ ውስጥ በንግድ እና የኢኮኖሚ አጋርነት ረገድ የአሜሪካን ሚና እንዳይተኩ ያስችላል ብሏል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶች ሳቢያ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ከሦስት ዓመት በፊት ከአጎዋ እንዳገዳት ይታወሳል። ኾኖም በአገሪቱ ላይ የተጣለው እገዳ ሳይነሳ ነው የአጎዋ የጊዜ ቆይታ ለሦስት ዓመታት የተራዘመው።