በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ባለፈው ሰኞ በቱርካዊያን ቱሪስቶች ላይ ታጣቂዎች የፈጸሙበትን ጥቃት የሚያጣራ አጣሪ ቡድን ተቋቋመ። አጣሪ ቡድኑ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከቱሪዝም ሚንስቴር፣ ከመከላከያ ሚንስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከደቡብ ምዕራብ ክልል ፖሊስ የተውጣጣ መሆኑን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን መናገራቸውን የቱርክ የዜና ወኪል ዘግቧል። አምባሳደር ባራን፣ ሁለት ቱርካዊያንና ኢትዮጵያዊ ሹፌራቸው ከተገደሉበት ጥቃት፣ ሌሎች ሁለት ቱርካዊያን ጎብኝዎች ከተሽከርካሪው ወጥተው በማምለጥ ነፍሳቸውን ማዳን ችለዋል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ከጥቃቱ ያመለጡት ሁለቱ ቱርካዊያን ጥቃቱን ለቱርክ ኤምባሲ በስልክ እንዳሳወቁ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ የሟቾቹ አስከሬን እና ከጥቃቱ ያመለጡት ቱርካዊያን ትናንት በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ገልጸዋል ተብሏል። የሟቾቹ አስከሬን ዛሬ ምሽት ወደ ቱርክዬ እንደሚላክ አምባሳደሩ እንደገለጡም ዘገባው አመልክቷል።