“የብልጽግና የቀይ ባሕር ፍላጎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው”- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የብልጽግና የቀይ ባሕር ፍላጎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው” አሉ።

ሰኞ ጥር 4/ 2018 ዓ. ም. በተላለፈው ቃለ ምልልስ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ካለው ውጥረት ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የውሃ ጦርነት ብሎ ማወጅ ለማን ነው? ለእኛ በቀጥታ የቀይ ባሕር ጉዳይ አይደለም። የናይል ጦርነት ነው እየታወጀ ያለው። ጦርነቱ ማንን የሚመለከት ነው?” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ለማግኘት የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም የፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴ ‘ለማዳመቅ’ የቀረበ ነው ሲሉም ከስሰዋል። ፕሬዝዳንቱ “ለጉዳዩ ዕውቅና መስጠትም አይገባም” ሲሉም አጣጥለዋል።

“ብልጽግና መጀመሪያ ላይ ጦርነት የከፈተው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ነው። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በአማራ ክልል ፋኖን ለማጥፋት ጦርነት ታውጇል። በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በሶማሊያ [ጦርነት ታውጇል]” ብለዋል።

አክለውም “ይህ ጨዋታ የብልጽግና አጀንዳ አይደለም። አጀንዳው የሌሎች ነው። ገንዘብ እየሰጡ እየደገፉት ያሉት ሌሎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ “እንዲህ ወዳለው ቀውስ የሚገፋፋ ሰነፍ፣ የከሰረ፣ ፈሪ እና ስግብግብ ነው” በማለትም ገልጸዋል።

ኢሳያስ ለጦርነት ዝግጅት ወደ ኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ሌሎችም የጦር መሣሪያዎች እየገቡ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

“ማነው ድሮኖቹን እያመጣ ያለው? ከውጭ እነዚህን ሁሉ መሣሪያዎች እየገዛ ያለው ማነው? ይሄንን ሁሉ ሴራ በገንዘብ እየደገፈ ያለው ማነው? ገንዘቡ ከየት ነው እየመጣ ያለው?” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ቃለ ምልልሱን ላደረጉላቸው ጋዜጠኞችም “ጊዜያችሁን አታባክኑ፤ እንዲህ ያለ ነገር በሚዲያችን መጠቀስም የለበትም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ጦርነት ከተከፈተብን ግን ማንም መብታችንን እንዲያስጠብቅ አንጠይቅም። ወደ ውሸት ጠረጴዛቸው መጋበዝ የለብንም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ ከመምጣቱ ባሻገር የጦርነት ስጋት ሲስተጋባ ቆይቷል። በተለይም ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ የጠለሸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት፤ ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ውጥረት ሰፍኖበታል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በሚያደርጉት ቃለ ምልልስ እንዲሁም የማስታወቂያ ሚኒስትራቸው የማነ ገብረመስቀል በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያወጧቸው ጽሑፎች ገዢው ፓርቲ ብልጽግናን ሲሸነቁጡ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ሆድ እና ጀርባ መሆናቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዋነኛነት ከግብፅ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረዋል።

ከግብፅ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ኤርትራ ስላላት ግንኙነት በሰጡት ማብራሪያ፤ በኤርትራ እና ሳዑዲ አረቢያ መካከል የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት “በጋራ መግባባት” ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የሚነሱ ችግሮች ዋነኛ መነሻቸው “የውጭ ጣልቃ ገብነት” መሆኑን ጠቅሰው “ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ያላቸው ሚና የጎላ መሆን አለበት” ሲሉም አክለዋል።

“የባሕር ዳርቻ እና የአየር ክልልን ኃያላን እንዲጠብቁት ማድረግ አይሠራም። ቀጣናዊ ደኅንነትን የሚያስጠብቀው ትብብር ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጽኑ በመተቸት የሚታወቁት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት በፈተና የተሞላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአሜሪካ ጋር የሚኖር ግንኙነት ከሁለትዮሽ ትስስር የዘለለ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

“ለአሜሪካ ምልከታችንን ማጋራት አለብን። ይህም የሁለትዮሽ ጉዳዩችን ብቻ የተመለከተ መሆን የለበትም። ስለ ቀጣናዊ ጉዳዮች፣ ስለ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን መነጋገር አለብን” ብለዋል።

“ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለእኛው ጉዳዮች ነው” ሲሉም አክለዋል።

ስለ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነትም አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ሱዳንን መቆጣጠር ከተቻለ፤ ግብፅ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራ እንዲሁም ቀይ ባሕር ላይ ጫና ለማሳደር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውክልና ጦርነት ነው” በማለት ተናግረዋል።

“የሱዳን ጦር ሊመሰገን እና ሊደገፍ ይገባል” ሲሉም እንደ ደቡብ ሱዳን ያለ ዕጣ ፈንታ ሱዳን እንዳይገጥማት መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ግብፅ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የጀመረችው የጎረቤት አገራት ውይይት ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም ድንገት መቋረጡንም ጠቅሰዋል።

“የሱዳን ጦር ሊደገፍ ይገባል። ተገዳዳሪዎቹ ላደረሱት ሞት እና ቀውስ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የሱዳንን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ዕድገት ማረጋገጥ የሁላችንም ፍላጎት ነው። ለሱዳናውያን ብለን ብቻ ሳይሆን ለሕሊናችን ስንል የምናደርገው ነው” በማለት አክለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር መካሰሳቸውን የቀጠሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ በዙሪያቸው ካሉ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክለዋል። በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ግብፅ፣ ሱዳን እና ሳዑዲ አረቢያ መጓዛቸውም አይዘነጋም።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን አጥብቀው ማንሳቸታው በኤርትራ በኩል ስጋትን ከመፍጠሩ ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

በአካባቢው ያላቸውን ተጽዕኖ ለማጠናከር ከተለያዩ አገራት እና ወገኖች ጋር ትብብራቸውን እያጠናከሩ ያሉት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፉክክር ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን በተደረገ ግብዣም ወደ ሱዳን አቅንተዋል።

በጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ ከሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር እየተፋለሙ ያሉት ጄኔራል አል ቡርሐን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጋር ወግነው ኢትዮጵያን ይቃወማሉ።

እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ትደግፋለች ከምትባለው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ኢትዮጵያ ባላት ወዳጅነት ምክንያትም ደስተኛ አይደሉም።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከተበላሸ በኋላ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ከምትወዛገበው ግብፅ ጋር ወዳጅነታቸውን አጠናክረዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ግብፅ ከማቅናታቸው በተጨማሪ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲም ወደ አሥመራ ሄደው ሶማሊያን የጨመረ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ትብብር መመሥረታቸው ይታወሳል።