የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ በቀይ ባሕር ላይ የሚያራምደው ፍላጎት ከናይል ወንዝ ጋር የተያያዘ መኾኑን ትናንት የኤርትራ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ተናገሩ።
“በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ “የውሃ ጦርነት ብሎ ማወጅስ ለማን ነው?” ጉዳዩ እኮ በቀጥታ የቀይ ባሕር ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም ብልጽግና ፓርቲ ያወጀው “የናይል ጦርነት ነው” በማለት እምብዛም ግልጽ ያልሆነ ማብራሪያ ሠጥተዋል። ኢሳያስ አያይዘውም፣ ሆኖም ለዚህ ጉዳይ “ዕውቅና” መስጠት አይገባም ሲሉ አጣጥለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ጦርነት አውጇል ያሉት ኢሳያስ፣ የፓርቲውን አጀንዳ በገንዘብ የሚደግፉት ግን የውጭ ኃይሎች ናቸው በማለት ከሠዋል።
ለጦርነት ዝግጅት፣ ድሮኖችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መኾኑን እንደሚያውቁም ፕሬዝዳንቱ ካሁን ቀደም የተናገሩትን ደግመውታል። የኤርትራ መንግሥት ጦርነት ከተከፈተበት ማንም መብቱን እንዲያስጠብቅለት እንደማይጠብቅም ተናግረዋል።