” ቀነኒ ቤት ውስጥ እንደሞተች ነው የምናምነው። … አስክሬኗን ከፍቼ አይቼው ነበር አስክሬኗ ላይ ምንም አይነት ስብራትም ሆነ ደምም ሆነ የተለያየ ጉዳት አልደረሰም ! ” – ለማ አዱኛ (ወንድም)
ከወጣቷ ቀነኒ አዱኛ ህልፈት ጋር በተያያዘ ድምፃዊ አንዱአለም ጎሳ በቅርቡ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ የተጠቀሱ የቀነኒ ወንድሞች ምላሽ ሰጡ።
አንዱ ስሙ የተጠቀሰው የቀነኒ አዱኛ ታናሽ ወንድም ሊበን አዱኛ ሲሆን አብሮ አንድ ቤት ከነሱ ጋር ይኖር እንደነበር ገልጾ የነበረውን አስረድቷል።
ቀነኒ አዱኛ በተደጋጋሚ ድብደባ እንደተፈፀመባት ከስልኳ የተገኙ ናቸው ካላቸው ምስሎች ጋር ያጋራ ሲሆን በተደጋጋሚ ሆዷና ልቧን በመረገጧም የመካንነት ምርመራ እስከማድረግ መድረሷን አሳውቋል።
ሊበን እህቱ ቀነኒና ድምፃዊ አንዱአለም ጎሳ መኖር በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የልደቷ ቀን የመጀመሪያ ድብደባ በአንዱአለም እንደተፈጸመባት ገልጿል።
ከዚህ በኋላም ቀነኒ እጇ ተሰብሮ መታሸጉን ከስልኳ ከተገኘው ፎቶ ጋር አጋርቷል።
በመቀጠል ከወራት በኋላ ቤት ውስጥ የነበረን ጊታር እንደሰበረ ሽጉጥም እንደተኮሰ አመልክቷል።
ሽጉጥ ተኩሶ በነበረበት ወቅት የነበረውን ክስተትም እንዲህ ሲል አስታውሷል ፦
” የዛን ቀን ተኝቼ ነበር ፤ አንድ ሰዓት አካባቢ ይሆናል።
እኔ ገስት ሩም ነበር የተኛሁት ቀነኒ ሮጣ ገባች እኔ ያለሁበት ክፍል ፤ በሩን ስትዘጋ የዛን ጊዜ ተነሳሁ።
ምንድን ነው ? ስላት ጊዜ ጊታሩን ወርውሮ ሲሰብረው ነበር የዛን ሰዓት ኮሪደሩ ላይ።
ከዛም ‘ ተነሳ ለማ ጋር ትሄዳለህ ‘ አለችኝ ምን ተፈጥሮ ነው ? ስላት ጊዜ አንዱአለም ሽጉጥ አቀባበለ በሩ ጋር ቆሞ። እኔ ላናግረው ስል ጊዜ ‘ አይሆንም ይመታሃል ብላ እሱ አይተኩስም አንተ ተረጋጋ እኔ አናግረዋለሁ አንተ እንዳትገባ በመሃል ‘ ብላ በሩን ከፍታ ወጣች።
በኋላም ሽጉጡን ፊቷ ላይ ደቀነባት ፤ የሆነ ፎቶ አሳያት ‘ ይሄ ፎቶ አንቺ ነሽ ? ‘ አላት፤ እሷ እኔ ‘ አይደለሁም ‘ አለች።
መፅሐፍ ቅዱስ ይዛ በጣም ማለችለት ‘ እኔ አይደለሁም እናቴ ትሙት ‘ ብላ። ‘ አንቺ ነሽ አላት ‘ ወደ ሚጣ (እህቱ) ዞረና ሚጣን ጠየቃት።
ሚጣም ‘ ኧረ እሷ አይደለችም ምን ሆነህ ነው አንዱአለም ‘ አለችው።
እኔን ጠየቀኝ እሷ አይደለችም ስለው ጊዜ እሷ ላይ ይዞት የነበረውን ሽጉጥ ወደ ሸተሩ አዙሮ ወደ ሸተሩ ተኮሰው። ”
–
አብረው በሚኖሩበት ወቅት አንዱአለም ለሊት ሊነጋጋ ሲል ቤት እንደሚገባ ፤ የዛን ሰዓት ከቀነኒ ጋር ጭቅጭቅ እንዳለ ፤ በዛ ሰዓት ሲመጣ ባህሪው እንደሚቀያየር ተናግሯል።
ሊበን ከኢሬቻ ኮንሰርት በኋላም ድምፃዊ አንዱአለም በብር ምክንያት ከሌላ ሰው ጋር ተጋጭቶ ቀነኒን እንደደበደባት ተናግሯል።
በቤቱ አብሯቸው በነበረበት ጊዜ ስለተፈጠረው ሌላ ክስተት እንዲህ ሲል ተናግሯል።
” ከመሞቷ ከወራት በፊት እኔ እዛ ቤት ነበርኩ።
ማታ መብራት የለም ነበረ አንድ ላይ እየተጫወትን ነበረ እሱም አብሮን ነበረ እህቱም ነበረች። አንድ ላይ እየተጫወትን ነበር።
4 ሰዓት አካባቢ እሱ የሚጠቃቀማቸው ነገሮች አሉት (የግል ሱሶች) እሱን ሊጠቀም ስለፈለገ ሚጣን ‘ አትተኚም ? ‘ ሲላት ጊዜ እኔ ፊት ማድረግ ስለደበረው ይሆናል ብዬ እኔም ገብቼ ተኛሁ ፤ ሚጣም ተኛች።
በመቀጠል ወደ ለሊት 10 ወይም 11 ሰዓት አካባቢ መሰለኝ በጣም ጭቅጭቅ ሰማሁ ስለምን እንደሆነ በደንብ አላውቅም በመሃል አልገባም ብዬ ለረጅም ሰዓት ቁጭ አልኩ፤ ከዛ የሆነ ሰዓት የሚወድቅ ነገር ሰማሁ።
ከፍቼ ስወጣ ቀጥታ በኮሪደሩ ላይ የነበረው አንዱአለም ነበር። ‘ በመሃላችን አትግባ ‘ ብሎኝ እኔን መልሶኝ በሩን ቆለፈው።
አምስት ደቂቃ ቆይቶ መጣና ‘ ክፈተው ሂድና አናግራት ‘ አለኝ ፤ በሩ ጋር ስሄድ ጥርሷ አካባቢ ደምቷል፤ ዝም ብላ ቁጭ ብላለች።
ሚጣን ቀሰቀሳት ከሚጣ ጋር ገስት ሩም አስገባናት። እንደዛ ሆና እኔን ስታየኝ ማለት እኔ እንደዛ ሆና ስላየኋት በጣም አለቀሰች እኔ እንደዚህ ሆኜኮ ብላ ማልቀስ ጀመረች። ”
–
ሊበን፣ ቀነኒ ከመሞቷ ከሳምንት በፊት የመካንነት ምርመራ አድርጋ እንደነበር ገልጿል።
የመካንነት ምርመራ ያደረገችው አቃቤ ህግ የሰጠው ወረቀት ላይ እንደተፃፈ ፤ በተደጋጋሚ ሆዷ እና ልቧ ላይ ተረግጣ ሃኪም ቤት ትመረመር እንደነበር እና ዶክተሩ ሲጠይቃት ‘ ሰው ነው የረገጠኝ ‘ እንዳለች ተናግሯል።
የአንዱአለም እናትም ቀነኒ ደውላላቸው መውለድ እንደምትችል እንደነገረቻቸው የገልጿል።
ሌላኛው የቀነኒ ወንድም ለማ አዱኛ ምን አለ ?
ድምጻዊ አንዷልም ጎሳ ቀነኒ ጭንቀት እንደነበረባት ፤ አጠቃላይ ያለውን ነገር ማንም ቀርቦ ጠይቆ የሚያውቅ ቤተሰብ እንደሌለ ተናግሮ ነበር።
ለማ አዱኛ ግን የቀነኒን ጭንቀት በተመለከተ ” ከእኛ ጋር በእሷ ህመም ዙሪያ የተማከርነውም የተወያየነውም ጉዳይ የለም ” ብሏል።
ቀነኒ ከመሞቷ በፊት ከምሽቱ 6:20 አካባቢ ደውላ በአንዱአለም ጎሳ ስም መኪና ለማስመጣት ፍቃድ እንዲያወጣ እንደነገረችው ይህን አውርተው በሰላም መለያየታቸውን አስታውሷል።
ቀነኒ ከሞተችበት ከለሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከቤት አንስተው ሚኒሊክ ሆስፒታል እስክትደርስ ድረስ ቤተሰቡ አለማወቁና ቤተሰብ ሳያውቅ ለመቅበር እቅድ እንደነበር ተናግሯል።
ለማ ” ከቤት አንስተው ያኔት ሆስፒታል ወሰዷት ‘ የእሷ ቅርብ ዘመዶች የሉም ? ‘ ሲባሉ ‘ እዚህ የላትም ገጠር ነው ያላት ‘ አሉ እዚሁ ከተማ ሆነን እንደሌለን ተደርገናል ” ሲል ገልጿል።
ሚኒሊክ ሆስፒታል ሁሉንም ነገር ጨርሰው እንደጠበቋቸውም ተናግሯል።
ሚኒሊክም አስክሬኗን በግድ ከፍቶ ማየቱን የተናገረው ለማ ” እኔ እስክሬኑን ከፍቼ ነው ያየሁት ፤ አስክሬኑ ላይ ምንም አይነት ስብራትም ሆነ ደምም ሆነ የተለያየ ጉዳት አልደረሰም ከዛ የሚያክል ፎቅ ላይ የወደቀ ሰው ደግሞ ይሰባበራል ብዙ ነገር ይደርስበታል ” ብሏል።
” ቀነኒ ቤት ውስጥ ነው የሞተችው፤ ሞታ አቅፈው መሬት ላይ አውርደው እራሷን ጥላ እንደሞተች አስመሰሉ ፤ ‘ ጮኸው ራሷን ጣለች ‘ አሉ ” በማለት እህቱ እንደተባለው ከፎቅ ላይ ወድቃ ሞታለች በሚለው እንደማያምኑ ተናግሯል።
” ጉማ “ን በተመለከተ ለማ ” አባገዳዎች ልኮ ጉማ እከፍላለሁ ሽምግልና አስታርቁኝ ብሎ ሲለምን ነበር ያልገደለበትን ጉማ የሚከፍልበት ምክንያት የለም። ከዛ ወጥቶ ግን ‘ እኔ ጉማ እከፍላለሁ አላልኩም ‘ በማለት የተናገረው ሃሰትና ማጭበርበር ነው ” ብሏል።
የቀነኒ ታናሽ ወንድም ሊበን በሰራው ቪዲዮ የተነሳ ማስጠንቀቂያ እየደረሰው መሆኑን ያነሳው ለማ አዱኛ በእሱም ሆነ በሌሎች ላይ የሆነ ነገር ቢደርስ ያደረሰው ” የምናውቀው ሰው ” ነው ብሏል።