የአፋብኃ ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ ከፍተኛ አመራር የሆነው ሻለቃ ሀብታሙ ደምሴ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ያስተላለፈው መልዕክት!!

“አንበሳ ምን ቢርበው ሳር አይግጥም!!”

የአፋብኃ ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ ከፍተኛ አመራር የሆነው ሻለቃ ሀብታሙ ደምሴ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ያስተላለፈው መልዕክት!!

የአማራ ህዝብ ላይ የተደቀነው የህልውና አደጋን ተከትሎ ለህዝባችን የደህንነት ዋስትና ለመሆን ዱር ቤቴ ብለን ጠብመንጃ አንስተን ወደ ጫካ እና በርሃ የገባነው ህዝብን የማዳን አላማን አንግበን መሆኑ ይታወቃል። በበኩላችን የምንሞትለትን አላማ ጠንቅቀን ስለምንረዳ ይህን አላማ ለማሳካት የሚያስችል ፅናት ተላብሰን ትግላችንን ቀጥለናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅርብ ወራጆች ደግሞ በየተራ ወደ ጠላት እየገቡ መሆናቸውን ታዝበናል።

ትግል ያለ አላማ እና ፅናት እንደማይሰምር ሁሉ፤ አላማ ቢስ የሆኑ ልፍስፍሶች ወደ ጠላት ሲገቡ ልንረዳው የሚገባ ነገር ቢኖር የትግሉ ሜዳ እየፀዳ መምጣቱን ነው። በትግሉ ሜዳ ላይ በፅናት መቆየት የሚችሉት አላማ ያላቸው ብቻ መሆናቸውን ልንገነዘብ ይገባል። አላማ ከሌላቸው ብዙኃን ይልቅ አላማ ያላቸው ጥቂቶች ለድል ይበቃሉ። የአማራ ህዝብ አሁን ላይ እየሆነ ባለው ነገር ሳይደናገር እና ሳይደናገጥ በእኛ በልጆቹ ሙሉ እምነት እንድኖረው የምናሳስበው የፀና ህዝብ አሸናፊ እንደሚሆን ስለምናውቅ ጭምር ነው። የትግሉ ሂደት መሰናክል የበዛበት መሆኑን አምነን መሰናክሎችን ሁሉ በፅናት ለማለፍ ቆርጠን እንደ ህዝብ መነሳት ይገባናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አማራዊ አንድነታችንን ማንበር ስንችል እና የጋራ መግባባት ላይ ስንደርስ ነው።

ባቡሩ ሲጓዝ በየፌርማታው የሚወርዱ ተሳፋሪዎች እንደሚኖሩ ተገማች ነው። ይህን ትግል እንደ ባቡር ቆጥረነው በየፌርማታው የሚወርደው ተሳፋሪ ጉዳይ ሊያሳስበን እንደማይገባ ለማስታወስ እንወዳለን::

በጣም የሚገርመው ነገር ቢኖር ወደ ጠላት የሚገቡ አካላት ለክዳታቸው እንደ ሰበብ የሚቆጥሩት በዋናነት ጌቶቻቸው የሚሰጧቸውን አጀንዳ መሆኑ ነው። ስለዚህ እነሱ ከጅምሩ የጠላት እንጅ የእኛ አልነበሩም ማለት ነው። የጠላትን አጀንዳ ከጠብመንጃ ጋር ተሸክመው ላይ ታች ሲሉ የነበሩ ስለሆኑ እነሱ ቢመጡ ቢሄዱ ምንም ሊደንቀን ሊጨንቀንም አይገባም።

ጥርሳችንን ነክሰን በመታገል የሚከፈለውን መስዋዕትነት እየከፈልን ለአማራ ህዝብ የደህንነት ዋስትናዎች ለመሆን እና ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግ ቆርጠን የተነሳን በመሆናችን እስከመጨረሻዋ የድል ብስራት ከአላማችን ዝንፍ እንደማንል እያረጋገጥኩኝ “አንበሳ ምን ቢርበው ሳር አይግጥም!!” እንድሉ አበው እኛም ምንም አይነት አጀንዳ ቢወረወር ከጠላት ጎን ልንሰለፍ እንደማንችል እሙን ነው።

ሻለቃ ሀብታሙ ደምሴ
የአፋብኃ ምኒልክ ዕዝ ከፍተኛ አመራር