በላስታ ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ኮር በተወሰደበት የማያዳግም እርምጃ የተበሳጨው የአገዛዙ ሰራዊት ንፁሃንን በከባድ መሳሪያ ጨፈጨፈ!

በላስታ ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ኮር በተወሰደበት የማያዳግም እርምጃ የተበሳጨው የአገዛዙ ሰራዊት ንፁሃንን በከባድ መሳሪያ ጨፈጨፈ!

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ ላስታ ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌ ኮር በጄኔራል ተፈራ ማሞ ክፍለ ጦር፣በእሸት ክፍለ ጦርና በነብሮ ተወርዋሪ ኮማንዶ ብርጌድ በላስታና ቡግና ሰንሰለታማ ተራሮች ሲቀጠቀጥ የዋለው የብልፅግና ወንበር አስጠባቂ ጦር በደረሰበት ሽንፈት ምላሽ ንፁሃንን በከባድ መሳሪያ ጨፈጨፈ።

መነሻውን ከአይና ቡግና አድርጎ 05 ቀበሌ ቅዱስ ሐርቤ (ጣንቋ) ላይ ታህሳስ 26/2018 ዓ/ም ንጋት አጥቢያ 12:00 ሰዓት እስከ ቀትር 8:00 ሰዓት ውጊያ የከፈተው የአገዛዙ ሰራዊት በጄኔራል ተፈራ ማሞ ክፍለ ጦር ሜካናይዝድና ሦስተኛና አራተኛ ሻለቃዎች በአይቆፍር ጨረሆና ሆዛ ሜዳ አቅጣጫ የመጣውን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተውታል፤በአውደ ውጊያው 35 የአገዛዙ ሰራዊት ሲደመሰስ ከ30 በላይ ቁስለኛውን በአምቡላንስና ፓትሮል እየለቀመ ተመልሷል እንዲሁም ሰባት አባላቱ የአማራን ህዝብ አንወጋም በማለት ከነሙሉ ትጥቃቸው ፋኖን ተቀላቅለዋል።

በዚህም የተበሳጨው የጁላ ሰራዊት ቡግና ወረዳ የ08 ቀበሌ ንብ ዋርካና የ05 ቀበሌ ቅዱስ ሐርቤ (ጣንቋ)ን ህዝብ በመድፍ፣በአየር መቃወሚያ(ዙ-23) እና በሞርታር-120 ሲጨፈጭፍ ውሏል፤በዚህ ጭፍጨፋ ሦስት ንፁሃን ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አራት የአርሶ አደር ቤቶች በዙ-23 ሲቃጠሉ ተጨማሪ ዘጠኝ ንፁሃን በከባድ ሁኔታ ቆስለው ህይወታቸው በህክምና እየተጠበቀ ይገኛል።

በጭፍጨፋው በከባድ መሳሪያ አንዲት የ60 ዓመት መነኩሴና የ15 ዓመት ልጃገረድ ለገና በዓልና ለንጉስ ላልይበላ ልደት ክብረ በዓል ወደ ላስታ ላሊበላ ይጓዙ የነበሩ እና ቅዱስ ሐርቤ ሚኒቃባ መንደር ከእናቷ ማዘል ላይ የነበረች እታቱ ሞላ ወዳይ የተባለች ህፃን ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ የህፃኗ እናትም ለህይወቷ አስጊ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በከባድ ሁኔታ የቆሰሉ:-
1ኛ. ደስታ ዋጋዬ የ28 ዓመት እናትና ልጆቿ መሰረት አበባው የ7 ዓመት ህፃን እንዲሁም ትዕግስት አበባው የ4 ዓመት ህፃን
2ኛ. ሐይማኖት ደማሙ የተባለች የ22 ዓመት ልጃገረድ
3ኛ. ወጋየሁ ባዬ የተባለች የ38 ዓመት እናት
4ኛ. እማሆይ አይቼሽ መልኬ የተባሉ የ75 ዓመት አዛውንት
5ኛ. መንበር አበባው የተባለ የ8 ዓመት ህፃን
6ኛ. ባየች ባዬ የተባለች የ28 ዓመት ወይዘሮ
7ኛ. ቄስ ካሳ ነጋሽ የተባሉ የ78 ዓመት የሐይማኖት አባት ቤተ-ክርስቲያን አገልግለው ሲወጡ እንዲሁም ህዝቡና አገልጋዩ በቅዱስ ሐርቤ ደብር ነዓኩቶልአብ ቤተ-ክርስቲያን እሁድ ሰንበትን እያከበረ በሚገኝበት በቤተ-ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ እንዳሉ በከባድ መሳሪያ ቆስለዋል ቤተ-ክርስቲያኑም ጉዳት አስተናግዷል።

በተያያዘም እሸት ክፍለ ጦርና ነብሮ ተወርዋሪ ኮማንዶ ብርጌድ ከላሊበላ ድብኮ ቀጠና በወሰዱበት የማያዳግም እርምጃ የአገዛዙ ሰራዊት በአፀፋው ንፁሃን ላይ መድፍ በመተኮስ ድብኮ ቀጠና ሁለት የአርሶ አደር ቤቶችን ያቃጠለ ሲሆን ስድስት ከብቶችም ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል።

መዳረሻው ድልና ነፃነት የሆነው የአማራ ህዝብ የህልውና ተጋድሎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲል የላስታ ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ኮር ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፋኖ መምህር ቢሆነኝ ቢያበይን መረጃውን አድርሷል!