“እየዘፈኑ ድህነት እያለቀሱ ክብረት”
በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከንጉሥ ሚካኤል አሊ ኮር የተሰጠ መግለጫ!
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ ንጉሥ ሚካኤል አሊ ኮር በሚንቀሳቀስባቸው ከደሴ ከተማ በስተምዕራብ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ የሰርግ ጥሎሽ አምስት ሺህ ብር ብቻ እንድሆን መወሰኑና በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል:: የመመሪያውን ተፈፃሚነት ይከታተል ዘንድ ኮሩ በየወረዳዎች የመደበው ግብረኃይል የሰበሰበው መረጃ እንደሚያስረዳው ህዝባችን ራሱ ያፀደቀውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ወይ መቶ ወይ መተው እየተባለ እስከ መቶ ሺህ ብር ድረስ ጥሎሽ በመጣል ገደብ የለሽ እና ድሀን አግላይ ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑን ደርሰንበታል:: ሰርግ ምስለት እየዘፈኑ ክስረት ሆኗል:: አላማውንም እየሳተ ነው!
በምድር በሰማይ እሳት እየነደደበት ያለው ህዝባችን በጦርነቱ ከደረሰበት የኢኮኖሚ ድቀት እና የማህበራዊ እረፍት እጦት በተጨማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ የሆኑ ባህላዊ ክዋኔዎች አሉ:: ከእነዚህ ባህላዊ አሰራሮች አንዱ የሆነው በተጋነነ ድግስ የሚከወን የሰርግ ስነ ስርዓት ነው:: ለሰርግ ብቻ ሳይሆን ለተዝካር እና ሰደቃ ያለ የሌለን ጥሪት አሟጦ የመደገስ ውሳኔ ከሀይማኖት ባሻገር ባህላዊ እየሆነ ነው:: ሐይማኖቶች በሚፈቅዱት መሰረት ተብቃቅቶ ህይወትን መምራትና አላስፈላጊ ወጭዎችን መቀነስ ተገቢ ስለሆነ ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ የንጉሥ ሚካኤል አሊ ኮር በሰርግ ዙሪያ መመሪያ አውጥቷል:: ይህ መመሪያ የሚደነግገው የሰርግ ጥሎሽ ከ 5 ሺህ ብር መብለጥ እንደሌለበት ነው::
መመሪያውን ተላልፎ የሚገኝ አካል 10 ሺህ ብር የሚቀጣ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከ5 ሺህ በላይ የከፈለው ገንዘብም ለፋኖ ገቢ ይሆናል:: ይህ ማለት አንድ ግለሰብ ለሰርግ ጥሎሽ በሚል 100 ሺህ ብር ቢከፍል 95 ሺህ ብር ለፋኖ ገቢ ሲሆን 5 ሺህ የሚሆነው ብር ደግሞ ለሴት አባት ይደርሳል ማለት ነው:: 10 ሺህ ብር ከፋይ የሚቀጣው ለህግ ጥሰቱ ማስተካከያ እርምጃ በማስፈለጉ መሆኑን ህዝባችን ከወዲሁ እንድገነዘብ ስንል ለማስታወስ እንወዳለን::
ስለዚህ ከዛሬው እለት ማለትም ከታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሰርግ ጥሎሽ 5 ሺህ ብር ሲሆን ከዚህ ቀደም ሌላ የገንዘብ መጠን ተጠይቀው የተወሰነ ፐርሰንት ከፍለው የነበሩት ደግሞ በውላቸው መሰረት ቀሪውን እንድከፍሉ ይገደዳሉ:: ከዛሬ ጀምሮ የሚፈፀሙ የጥሎሽ ስምምነቶች ጣራ ግን 5 ሺህ ብር ብቻ መሆኑ ይታወቅልን ሲል የንጉሥ ሚካኤል አሊ ኮር ሰብሳቢ ሻለቃ አብነው ታደሰ አሳስቧል::
©አፋብኃ ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ