በምሥራቅ ወለጋ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል የተፈጸመ የ19 ሰዎች ግድያ እና በስጋት ውስጥ ያሉት ነዋሪዎች

የጊዳ አያና ወረዳ ከተማ

የፎቶው ባለመብት,GIDA AYANA COMMUNICATION

የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱ የተፈፀመበት አካባቢ ከጊዳ አያና ወረዳ ዋና መቀመጫ አያና ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ “በኦሮሚያ ልዩ ኃይል” ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት 19 ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ደግሞ መቃጠላቸውን እና መዘረፋቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ተቃዋሚዎቹ እናት ፓርቲ እና ኢህአፓ ጥቃቱ “በመንግሥት መዋቅር የተፈጸመ” መሆኑን በመግለጽ ሲያወግዙት የክልሉ እና የአካባቢው ባለሥልጣናት አስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም።

በወረዳው የአማራ ተወላጆች ይኖሩበታል በተባለው ጠጋ ጂጊ (ሻሾ በር) አነስተኛ ከተማ ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም. አንድ መነኩሴን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በስለት እና በጥይት “በአሰቃቂ ሁኔታ” ተደብድበው መገደላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የዐይን እማኞች እና የሟች ቤተሰቦች አስታውቀዋል።

ከጥቃቱ ሁለት ቀናት አስቀድሞ በአካባቢው ለወራት የቆየው የመከላከያ ሠራዊት ለቅቆ ሲወጣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል የሆነው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል (ልዩ ኮማንዶ)” መግባቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ማክሰኞ ታኅሣሥ 14 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የተኩስ ልውውጡ በማን መካለል እንደተደረገ እንደማያውቁ አንድ ነዋሪ ሲናገሩ፤ ሌላ ነዋሪ ደግሞ መሳሪያ አናስረክብም ብለው ጫካ በገቡ እና ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች እና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል መካከል ውጊያ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን በአካባቢው ግጭት እንደነበር የሚጠቁም መረጃዎችን አውጥተዋል።

ግጭቱ ከመቀስቀሱ አስቀድመው ስጋት ያደረባቸው እና ከተቀሰቀሰ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ቀበሌዎች መሸሸታቸውን ጠቁመው፤ ውጊያው እስከ እኩለ ቀን ድረስ መቆቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ይደርስብናል ያሉትን ዛቻ መሠረት አድርገው ባደረባቸው ስጋት መከላከያ ሠራዊት ሲወጣ ቤተሰባቸው እንዲሸሽ እንዳደረጉ የተናገሩ አንድ የዐይን እማኝ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲመለሱ እልቂት እና ውድመት መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በቃ ቤቶች ወድመዋል፤ ጠቅላላ ወድመዋል” ያሉት እማኙ የሁለት ሰዎች አስከሬን ማየታቸውን ገልጸዋል።

የደረሱ ነፍሰ ጡር በመሆናቸው የተኩስ ልውውጡ ሲደረግ ቤታቸው እንደነበሩ የተናገሩ አንድ የዐይን እማኝ ከሟቾቹ ውስጥ የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ባለቤታቸው እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ሦስት “አረንጓዴ ቡራቡሬ” የደንብ ልብስ የለበሱ “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል” አባላት እና አንድ ሚሊሻ ቤታቸው መጥተው የጉልበት ሠራተኛ የነበሩትን ባለቤታቸውን ዐይናቸው እያየ በአቃቂ ሁኔታ እንደገደሏቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እኔ ድንጋይ ሆንኩኝ፤ ልጆቼ እየተንጫጩ እላዩ ላይ ሲወድቁ፤ ‘አምጣው መሳሪያውን እመታቸዋለሁ’ ሲል እኔ በጥርሴም መሰለኝ ያነሳኋቸው፤ ሦስቱንም [ልጆች] አነሳኋቸው። ተደፍቼ እኔን ግደሉኝ ብዬ ለመንኳቸው” ሲሉ ስለ ድርጊቱ ተናግረዋል።

ባለቤታቸው ቤታቸው በር ላይ በተገደለበት ስፍራ ከተቀበሩ ከአምስት ቀናት በኋላ ሥላሴ በተባለ ቤተ ክርስቲያን ዳግም መቀበራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች እና የሟች ቤተሰቦች ጥቃቱ የተፈፀመው የተኩስ ልውውጡ ጋብ ሲል ቤታቸው ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና ወደ ቤታቸው እየተመለሱ በነበሩ ንፁሃን ሰዎች ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

እማኞች አብዛኞቹ ሟቾች በስለት (ቢላዋ) ተጠቅተው መገደላቸውን እና አስከሬናቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተቆራርጦ እና ተጎድቶ መገኘቱን ተናግረዋል።

አንድ የቤተሰባቸው አባል የተኩሱ ልውውጥ ጋብ ሲል ቤታቸውን ለማየት ሲመጡ መንገድ ላይ እንደተገደሉባቸው የተናገሩ ሁለት ሰዎች፤ “አካላትም የለው” ሲሉ አስከሬናቸው ከባድ ጉዳት ደርሶበት ከቀናት በኋላ መገኘቱን ገልጸዋል።

የጊዳ አያና ወረዳ ከተማ

የፎቶው ባለመብት,GIDA AYANA COMMUNICATION

የምስሉ መግለጫ,የጊዳ አያና ወረዳ ከተማ

“የሞቱትን እንኳ ደርሰን ለመቅበር እና አስከሬን ለማንሳት አልቻለንም። እስከ ቅዳሜ ዕለት ድረስ አስከሬናቸው እንዳልሆነ ሆኖ [አገኘናቸው]” ሲሉ አንድ እማኝ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ካነጋገራቸው አምስት ነዋሪዎች እና የሟች ቤተሰቦች ውስጥ አራቱ በጥቃቱ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎችን ቁጥር 19 ነው ሲሉ አንድ ነዋሪ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል።

አንድ ነዋሪ ለጥቃቱ ምክንያት ነው የሚሉትን ለቢቢሲ ሲያጋሩ “የእናንተ ልጆች ናቸው ከፊደራል መንግሥቱ ጋር የገጠሙት። ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል ነው ብለዋል።

እናት ፓርቲ እና ኢሕአፓ ጥቃቱን አውግዘው ባወጡት መግለጫ ጥቃቱን “በመንግሥት መዋቅር በግልፅ” የተፈፀመ እና “በእጅጉ የሚያሳዝን ተግባር” ብለውታል።

ጨምረውም ይህ ተግባር “መንግሥት በዓላማና በስውር የሚፈጽም ደባ በመሆኑ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጭፍጨፋውን እንዲያወግዝና ተጠያቂነት እንዲሰፍን” የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

ባለቤታቸው የተገደለባቸው ነፍሰ ጡር ነዋሪ “መሬት የለኝ፣ ምን የለኝ፤ እሱ ነው የቀን ሥራ ሠርቶ የሚያስተዳድረኝ። አምስት ልጅ ይዤ የምልሰው የምቀምሰው አንድ ነገር እንኳ የለኝም” ሲሉ መፃኢ ሁኔታቸውን በሚመለከት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“[ባለቤታቸው] እሱን እንዲህ ሆኖ ስላገኘሁት ምግብ ትቻለሁ፤ ተጎድቻለሁ” ሲሉ አሁን ያሉበትን ሁኔታ አንድ የሟች ቤተሰብ ተናግረዋል።

በአካባቢው መከላከያ ሠራዊት ተመልሶ የገባ ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡ ስጋት እና ጭንቅ ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

አንድ የሟች ቤተሰብ “አሁንም መጡ እየተባለ ሰው እየተሸበረ ነው ያለው። መኖር አይደለም የምንኖረው። . . . ስጋት ላይ ነው ያለነው፤ ምጥ ላይ ነው ያለነው” ብለዋል።

“ያለፈው ሳይሆን እኛን እያሳሰበን ያለው ወደፊት የሚመጣው ነገር ነው። አሁንም ቢሆን በቅርብ ርቀት አሉ። መውጫ የለንም፤ ግራ ቀኝ በር ተዘግቷል” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ቢቢሲ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እና የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ አዛዥን ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።

ጊዳ አያና ወረዳ ከዞኑ ዋና ከተማ ነቀምቴ በ100 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚርቅ ወረዳ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ወረዳው የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን የሚያዋስን አካባቢ ሲሆን በድንበር አካባቢም ፋኖ ነን የሚሉ ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ እና ጥቃት እንደሚፈጽሙ ይነገራል።