ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በጎርጎርዮሳውያን /Gregorians/ የዘመን አቆጣጠር በነገው ዕለት የሚጀመረውን የ2026 አዲስ ዓመት በማስመልከት ለመላው የዓለም ማኅበረሰብእ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት
ቅዱስነታቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት የአማርኛ ትርጉም እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ለመላው የዓለም ሕዝብ የተላለፈ
አባታዊ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት፡-
እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።”
(ሉቃ. 2፡11)
የጌታችን ልደት የሰው ልጆች ምኞት የተፈጸመበት ፣ ከሁሉ በላይ የእግዚአብሔር ፍቅርና ማዳን የተገለጠበት በመሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ሲያስቡት ይኖራሉ፤ አዲስ ዘመንም ካለፈው ዓመት የቀጠለ የቍጥር ቀመር ሳይሆን እያንዳንዱ ቀን የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እናምናለን፤ በዘመን ላይ ዘመን ሲጨመር ገንዘብ ሊገዛው፣ ሥልጣን ሊያመጣው የማይቻለውን የዕድሜ ስጦታ አግኝተናልና የምስጋና ርእሳችን ነው ። እያንዳንዱ ዘመን ይዞት የሚመጣው በረከት፣ ትምህርትና ብስለት ያለው በመሆኑም በመላው ዓለም ሆናችሁ እንደየዘመን አቆጣጠራችሁ የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለምታከብሩ፤ እንዲሁም የ2026ን አዲስ ዓመት ለመቀበል ለተዘጋጃችሁ ወገኖቻችን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን ።
በአዲስ ዘመን ተነፋፍቆ የቆየው ወዳጅ የሚገናኝበት ፣ ወደ ቤቱም የሚመለስበት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዘመን ብዙ ልዩነቶች ዓለምን እያወኩ ይገኛሉ፤ የበዓሉ ዓላማ ግን መገናኘት በመሆኑ ወደ አንድነት መምጣት አስፈላጊ ነው። ሁሉን የሚያስተባብር ደስታ በዓለም ላይ የለም ፣ የክርስቶስ መወለድ ግን ሰማይና ምድርን፣ ሰዎችና መላእክትን ለዝማሬ ያገናኘ፣ ሰላምን ዓላማ ያደረገ ታላቅ መገለጥ ነው ። ዛሬም የምንኖርባት ዓለም በዚህ የጌታችን ልደትና የ2026 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ስለ ሰላም ማሰብ ይጠበቅባታል፤ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ሕዝቦች፣ የሩሲያና የዩክሬን ወገኖቻችንም ዘላቂ ሰላም ሊያገኙ ይገባቸዋል ።
በየስፍራው የሚገደሉና የሚታገቱ፣ እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነትና ሃይማኖት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ተጠቂዎችን ለመታደግም ጊዜው አሁን ነው ። በስደት ዓለም ላይ ተጨማሪ ስደት የገጠማቸውን ወገኖች መጠጊያ መስጠት፣ ዓለም ጊዜያዊ ቤት መሆኗን አምኖ እርስ በእርስ መረዳዳት ይገባል ። በዚህ ወቅትም ከዘመድና ከወዳጅ ርቀው ያሉት የሰዎችን ፍቅር ስለሚፈልጉ በክርስቶስ የምታምኑ፣ በበጎነት የምትደሰቱ ሁሉ ወገን ለሌላቸው ወገን ትሆኑ ዘንድ እንመክራለን።
የተወደዳችሁ የዓለም ሕዝቦች!
ክርስትና ለዓለም ትልቅ ብርሃንን ያበሰረ ፣ የሞራል ልዕልናን የሰበከ ፣ ከሁሉ በላይ በማዳን እውነት የሚጀምር ሃይማኖት ነው ። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ክርስትናን የሚከተል ቢሆንም ይህ ክርስትና በዘመናችን በተለያዩ አካላት ሲገፋ እየተመለከትን ነው፡፡ ለአብነትም ክርስቲያኖች በየስፍራው ይታገታሉ፤ ይገደላሉ፤ ስልጣኔው ብዙ ምቹ ነገሮችን ያመጣ ቢሆንም ለክርስትናው ግን ምቹ ያልሆነ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ባለማወቅም ሆነ በዓላማ ክርስትናን ለማዳከም እና ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ከክፉ ድርጊታቸው እንዲመለሱ አበክረን እናሳስባለን፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሰውን የሃይማኖት መብት ለማስከበር የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም መጪው ዘመን ችግረኞች የምግብና የደኅንነት ዋስትና የሚያገኙበት፣ የተለያዩት የሚገናኙበት፣ የጦርነት ቀጠሮዎች የሚሰረዙበት፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት፣ የዓለም ኢኮኖሚ ከፍ የሚልበት፣ ክብር የሚመለስበት፣ መሪዎች በጥበብ የሚያስተዳድሩበት፣ ሕዝቦች በትሕትና የበላዮቻቸውን የሚያከብሩበት፣ ከሁሉ በላይ ፍቅር በእያንዳንዱ የዓለም ጎጆ ውስጥ የሚገባበት እንዲሆን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን፤ እንዲሁም መላውን ዓለም ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
© የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት