እስራኤል ለሶማሌላንድ ከሰጠችው የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በኋላ ዛሬ የመጀመሪያውን ስብሰባ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት “የት ደረሰ?” የሚል ጥያቄ አነሳ።
በመደበኛ ስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስም ሆነ ምክትሎቻቸው ከሶማሌላንድ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ጥያቄውን ካነሱት የፓርላማ አባላት አንዱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት እንደቀሩት አስታውሰዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ የ20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ በኪራይ ውል ማግኘት የሚያስችላት እንደነበር አንስተዋል።
በምትኩም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል የመጀመሪያዋ በመሆን ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት ተስማማታ እንደነበር ገልጸዋል። ይሁንና ኢትዮጵያ “የባሕር በሩን ሳታገኝ እና ለሶማሌላንድ እውቅና ሳትሰጥ” በእስራኤል መቀደሟን ዶ/ር አበባው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት “ሁለተኛዋ ሀገር” ትሆን እንደሆነም የፓርላማ አባሉ ጠይቀዋል።
ዘገባው የኢትዮ ኢንሳንደር ነው!