ከሶማሊያ በተናጥል ውሳኔ የተገነጠለችው ሶማሊላንድ ከ30 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በኋላ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. እስራኤል ሰጥታለች። ሶማሊላንድ እውቅናውን ያገኘችው፣ እስራኤል እና ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ በነደፉት “የአብርሃም ስምምነት” ማዕቀፍ አንዳቸው ለሌላኛቸው እውቅና ለመስጠት እና ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸውን ተከትሎ ነው።
ዕውቅናው የሶማሊላንድን ሕዝብ በደስታ ሲያስፈነድቅ፣ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ የዘለቀ ብርቱ ተቃውሞም ቀስቅሷል።
የሶማሊላንድ የዕውቅና ጥያቄ አነሳስና ጉዞ
የሶማሊላንድ የሉዓላዊ አገርነት የዕውቅና ጥያቄ በአውሮፓውኑ 1960 ከብሪታንያ እንዲሁም ደቡባዊቷ ሶማሊያ ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ በወጡ ማግስት የሚጀምር ነው። ሶማሊላንድ ከብሪታንያ ነጻ በወጣች በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍቃዷ ከሶማሊያ ጋር ተዋሃዳ ነበር። በእነዚያ አጭር ቀናት ውስጥ እንደ ሉዓላዊ አገር ካወቋት ከ30 በላይ አገራት መካከል አንዷ እስራኤል ነበረች።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በግዛቲቷ አብላጫ ቁጥር ያለው የኢሳቅ ጎሳ አማጺ ቡድን የማዕከላዊውን የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ወታደራዊ መንግሥት አፈና እና መድልዖ በመቃወም የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀመረ። ሶማሊያም በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች። ቡድኑ ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመተባበር የዚያድ ባሬን መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1991 ከጣለ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ነበር ሶማሊላንድ ነጻ አገር መኾኗን ያወጀችው።
ከዚያም ሶማሊላንድ በ2001 (እአአ በመጀመሪያው ፕሬዝዳንቷ መሐመድ ኢጋል አመራር በ97 በመቶ ድምጽ የግዛቲቱን ነጻነት የሚያውጀውን ሕገመንግሥት በሕዝበ ውሳኔ አጽድቃለች። በዓለም አቀፍ ሕግ ይፋዊ የነጻ አገርነት ጥያቄዋ የሚጀምረው ያኔ ነው።
ግዛቲቱ በዚሁ ሕገመንግሥቷ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዘርግታ በርካታ ምርጫዎችን አካሂዳለች። ሶማሊያ በጦር አበጋዞች እና ከዚያም በእስላማዊ አክራሪ ቡድኖች አማካኝነት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በገባችባቸው ዓመታት ሁሉ፣ ሶማሊላንድ ባንጻሩ ባሰፈነችው መረጋጋት፣ በተከታታይ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎቿ እና በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለአፍሪካ ቀንድ ምሳሌ ተደርጋ ስትቆጠር ነው የኖረችው።
ግዛቲቱ ለዓለም አቀፍ ዕውቅና መስፈርቶች የሆኑት ማዕከላዊ መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይል፣ የታወቀ ድንበር እና በግዛቷ ውስጥ የሚኖር 5 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ቢኖራትም፣ እውቅና ለማግኘት ያደረገችው ብርቱ ጥረት ግን ሳይሳካ ዓመታት ነጉደዋል። ለዚህም የሶማሊያ ብርቱ ተቃውሞ፣ የቀጣናዊ እና የዓለም ኃያላን አገራት ተቃራኒ ፍላጎቶች እና የቅኝ ግዛት ድንበሮች ጸንተው እንዲቀጥሉ የሚጠይቁት የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ሆኖም የሶማሊላንድ መሪዎች የዚያድ ባሬ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርሷል የሚለውን ትርክት፣ የአገርነት እውቅናውን አስፈላጊነት ሕዝባቸውን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብን ለማሳመን እንዲሁም ከሶማሊያ የተለየ ሥነ ልቦና እና ማንነት ለመገንባት ተጠቅመውበታል።
ሶማሊላንድ ለዓመታት ዕውቅና ባታገኝም፣ በተለይ ከኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከብሪታኒያ እና ከታይዋን ጋር ጠበቅ ያለ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና ፀጥታ ግንኙነት መመሥረት ችላለች። ሶማሊያም ግዛቲቱን በሰላማዊ መንገድም ይሁን በኃይል ለመጠቅለልም ሆነ ነጻ መንግሥትነቷን ለመሸርሸር በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቻቸውን ሕግጋት ተፈጻሚ ማድረግ አልቻለችም። ሶማሊላንድ እና ሶማሊያ ውዝግቡን ለመፍታት ያደረጓቸው የድርድር ሙከራዎችም ፍሬ አላፈሩም።
የሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ ይበልጥ መነጋገሪያ የሆነው፣ ግዛቲቱ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመስጠት እና በምላሹ የኢትዮጵያን እውቅና ለማግኘት በ2024 የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመች ጊዜ ነበር። ሆኖም ሶማሊያ እና የሶማሊያ አጋሮች በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ፣ በቱርክ አሸማጋይነት ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት መቀበሏን በይፋ ማረጋገጧ አይዘነጋም።
ከዚያ ቀጥሎ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ለሶማሊላንድ ዕውቅና ሊሠጥ ስለማቀዱ በሠፊው ሲዘግብ የቆየ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ የሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ መፍትሄ እንደሚያገኝ መጠቆማቸው የሚታወስ ነው። የትራምፕ አስተዳደር ሶማሊያ ለዓመታት መረጋጋት ባለመቻሏ ድጋፉን መቀነስ የጀመረ ሲሆን፣ “የአንዲት ሶማሊያ” ፖሊሲውን ግን እስካሁን በይፋ አልቀየረም።
የፎቶው ባለመብት,@netanyahu/x
ዕውቅናው ለሶማሊላንድ ያለው አንድምታ
የእስራኤል እርምጃ በመላው አፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአረቡ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ የጂኦፖለቲካ ለውጥ ሊያስከትል እና ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ሊፈጥር የሚችል ነው።
ከሶማሊላንድ አንጻር ዕውቅናው ሶማሊላንድ ከሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ዕውቅና እንድታገኝ በር ሊከፍትላት ይችላል። እስራኤልም እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሷ በፊት ከተወሰኑ የአፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ምዕራባዊያን አገራትን ይሁንታ ለማግኘት ጥረት አድርጋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን ስኢድ አቡ ሃሺምም፣ አሜሪካ እና የምዕራብ አውሮፓ አገራት ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ጠቁመዋል። አብዱራህማን ያ እስኪሆን ግን የአንድ አገር ዕውቅና ብቻውን ብዙም ለውጥ አያመጣም ባይ ናቸው።
የስምምነቱ ዝርዝር ለጊዜው በይፋ ባይታወቅም፣ ዕውቅናው ግዛቲቷ ከእስራኤል የልማት፣ የቴክኒክ ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት ብሎም የወታደራዊ አቅም ግንባታ ድጋፍ ሊያስገኝላት ይችላል።
ሶማሊላንድ በምላሹ ለእስራኤል ምን እንደምትሰጥ ለጊዜው ይፋ ባይሆንም፣ የጋዛ ፍልስጤማዊያንን ተቀብላ ለማስፈር ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር በምሥጢር ተስማማታለች የሚሉ ዘገባዎች ከወራት በፊት ወጥተው ነበር። የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ግን በወቅቱ መረጃውን አስተባብለዋል። እስራኤል ዕውቅና በሰጠችበት ይፋዊ መግለጫዋም ይህንን ጉዳይ አላነሳችም።
ሶማሊላንድ ዕውቅናውን ያገኘችው፣ ከፑንትላንድ የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳባቸው “ሰናግ”፣ “ሱል” እና “ካይን” በተባሉ ምሥራቃዊ አውራጃዎች ከሶማሊያ ጋር መዋሃድ የፈለጉ የዱልበሃንቴ ጎሳ ሚሊሻዎች ከግዛቱቱ ሠራዊት ተዋግተው፣ ካሸነፉ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።
ሚሊሻዎቹ የአካባቢውን ዋና ከተማዋ ላስ አኖድን በ2023 ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ “ካቱሜ” ሲሉ የሰየሟት አዲሷ ፌደራል ግዛት ከወራት በፊት የሶማሊያን ፌደሬሽን ተቀላቅላለች። በተለይ የግጭቱ ደም አፋሳሽነት፣ በሶማሌላንድ የእውቅና ጥያቄ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዚህ ሁኔታ የሶማሊላንድ ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ በነበረበት ወቅት ላይ ነው እንግዲህ እስራኤል ዕውቅና የሰጠቻት። የሶማሊላንድ እና የእስራኤል ስምምነት በተለይ ወታደራዊ ትብብርን የሚያካትት ከሆነ፣ ሶማሊያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በውክልና ግጭት እንዳታዳክማት ዕድል ሊፈጥርላት ይችላል።
ቀጠናዊ አንድምታ
ከሶማሊያ አንጻር፣ ሶማሌላንድ ዕውቅና ማግኘቷን አል ሸባብ ይበልጥ ሶማሊያዊያንን ለማነሳሳት ሊጠቀምበት ይችላል ብለው የሚሰጉ ወገኖች በርካቶች ናቸው። ይህ ከሆነ፣ ጉዳዩ ሶማሊያን ጨምሮ የባሰ ቀጠናዊ አለመረጋጋት ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም።
ፑንትላንድ እና ጁባላንድ ራስ ገዞች ከሞቃዲሾ ጋር በገቡበት ፖለቲካዊ እና ሕገመንግሥታዊ ውዝግብ ሳቢያ፣ ከፌደሬሽኑ ለጊዜው በወጡበት ሁኔታ ውስጥ ሶማሌላንድ ዕውቅና ማግኘቷ ሁኔታውን ለሶማሊያ ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ፑንትላንድ ከሶማሊላንድ ጋር የነበራትን ቁርሾ አርግባ የፀጥታ ትብብር እስከመፈራረም ደርሳለች።
ከአፍሪካ ቀንድ፣ የሶማሊላንድ ዕውቅና ማግኘት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር ስምምነት እንዲያንሠራራ ሊያደርግ ይችላል። ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት ለማክበር ብትስማማም፣ የባሕር በር ስምምነቱን ስለመሠረዟ ግን በይፋ አልገለጠችም።
የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማንም፣ የእስራኤል ዕውቅና ለኢትዮጵያ ጥሩ አበረታች ዜና ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት አላቸው። የእስራኤል ወደ ሶማሊላንድ መምጣት በእርግጥም ለኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ላይ ከኤምሬቶች በተጨማሪ ሌላ አጋር ያስገኝላታል።
በቀጠናው ከሶማሊላንድም ከሶማሊያም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲያደርጉ የቆዩት በዋናነት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ሲሆኑ፣ ባንጻሩ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ጂቡቲ ግንኙነታቸው ከሞቃዲሾ ጋር ነው።
በተለይ ሱዳን ጠንካራ ፀረ-እስራኤል አቋም በማራመድ ነው የምትታወቀው። በተለይ ጂቡቲ ሶማሊላንድ ወደፊት የኃያላን አገራትን ዕውቅና ካገኘች፣ በወደብም ሆነ በወታደራዊ ጦር ሠፈርነት እንዳትቀናቀናት ትሠጋለች።
አፍሪካ ኅብረት እስራኤልን በስም ሳይጠቅስ የሶማሊላንድ ዕውቅና ለአህጉሪቱ “አደገኛ ምሳሌ” ነው በማለት ውድቅ አድርጓል። ኅብረቱ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እኤአ በ1964 በደረሠበት ውሳኔ መሠረት አባል አገራት በቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ የወረሱት ድንበር የጸና ነው በማለት ነው ተቃውሞውን የገለጸው።
የአፍሪካ ኅብረት አንዱ አጣብቂኝ፣ እኤአ በ2005 በሶማሌላንድ የዕውቅና ጥያቄ ዙሪያ ጥናት እንዲያደርግ ወደ ግዛቲቷ የላከው ልዑክ ባወጣው ሪፖርት፣ የሶማሊላንድ ጥያቄ “በታሪክ ለየት ያለ” እና “በአፍሪካ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ አሳማኝነት ያለው” በማለት የደመደመ መሆኑ ነው።
ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ውህደቱን በሕጋዊ መንገድ እንዳላጸደቁት ልዑኩ በሪፖርቱ ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ ሶማሊላንድ “የዲሞክራሲያዊ መንግሥትነት መሠረቶችን” መጣሏንም በመጥቀስ ኅብረቱ የግዛቲቱን ጥያቄ የሚያስተናግድበት “ልዩ ዘዴ” እንዲፈልግ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
ሆኖም ኅብረቱ ይህንኑ የራሱን ድምዳሜ ችላ ብሎ የእስራኤልን እውቅና ማውገዙ ፖለቲካዊ እንጅ ሕጋዊ መሠረት የለውም በማለት የሚተቹት ወገኖች አሉ።
የፎቶው ባለመብት,AFP
ሶማሊላንዳዊያንም፣ የሶማሌላንድ ነጻነት ወደ ቀድሞ ሉዓላዊቷ መመለሷን እንጂ ከመገንጠል ጋር ግንኙነት ስለሌለው የአፍሪካ ኅብረትን ቻርተር አይጥስም በማለት የሚካራከሩት፣ አፍሪካ ኅብረት እንዳመነውም ውህደቱ እንዳልጸደቀ በመጥቀስ ጭምር ነው።
እስራኤል ለግዛቲቷ የሰጠችው ዕውቅና፣ አፍሪካ ኅብረትን ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል። የእስራኤል ውሳኔ፣ አፍሪካ ኅብረት ለእስራኤል የሰጣት የታዛቢነት መቀመጫ እንዲነሳ ለሚፈልጉ አገራት ተጨማሪ እርሾ በመሆን፣ የኅብረቱን አባል አገራት ይበልጥ ሊከፋፍል የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም።
ሶማሊላንድ የዓለም አንድ ሦስተኛው ነዳጅ ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ አውሮፓ እና እስያ በሚተላለፍበት ባብኤል መንደብ ሠርጥ አቅራቢያ መገኘቷ እና ቦታው ለኢራን እና ለየመን ቅርብ መሆኑ ነው ለእስራኤል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋን ያጎላዋል።
እስራኤል ከሶማሊላንድ ጋር በአገር ደረጃ ትብብር መጀመሯ፣ በኤደን ባሕረ ሠላጤ ላይ ወታደራዊ ጣቢያ እንዲኖራት በር ሊከፍትላት ይችላል። በዚህም እስራኤል የቀይ ባሕር አዋሳኝ ሳትሆን በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተዋናይ እና የቀጣናው ኃያላን የሆኑት የግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ተገዳዳሪ ነው የምትሆነው።
የየመን ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃቶችን መፈጸም ከጀመሩ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገባች ወዲህ፣ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንድትሰጥ የውጭ ፖሊሲ ተንታኞቿ ሲወተውቱ ነበር።
ኢራንም ባለፉት ዓመታት በፖርት ሱዳን ዳርቻ ላይ ወታደራዊ መቆናጠጫ ጣቢያ ለመገንባት የሱዳን መንግሥትን ስታግባባ እንደቆየች ይነገራል። ኢራን ከእስራኤል የአየር ድብደባ በኋላም፣ ቁጥር አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ስጋት ሆና እንደምትቀጥል እና ወታደራዊ አቅሟንም መልሳ በመገንባት ላይ መሆኗን በርካታ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማንም፣ የእስራኤል ምሁራን ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አላት ለሚሏት ሶማሊላንድ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ መንግሥት ዕውቅና አንዲሠጥ ሲወተውቱ አንደነበር ጠቀሰው፣ ሆኖም እሰራኤል የመጀመሪያውን ትነሳሽነት የምትወስድ አገር ትሆናለች ብለው አልጠበቁም ነበር።
ከመካከለኛው ምሥራቅ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚያውቁ እና ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በተለይ ግብፅ እና ቱርክ ከሞቃዲሾ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ቱርክ፣ ሶማሊላንድን የሚያካትተውን የሶማሊያን የባሕር ወሰን ጭምር በባሕር ኃይሏ ለመጠበቅ ነው ውል የፈረመችው።
የእስራኤል ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣት፣ በተለይ ቱርክ በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ የሚገዳደር እና ከእስራኤል ጋር ሽኩቻ ውስጥ የሚያስገባት መሆኑ አይቀርም። ለዚህም ነው ግብፅ እና ቱርክ ፈጥነው የእስራኤልን ውሳኔ ያወገዙት።
በአንጻሩ “የአብርሃም ስምምነትን” ቀድማ የተቀበለችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከሶማሊላንድ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ በርበራ ወደብን የሚያስተዳድረው ግዙፉ የዱባዩ የወደብ ኩባንያዋም ወደቡን ለማስፋፋት እና ከኢትዮጵያ ጋር ለማስተሳሰር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል።
አሜሪካ እና ቻይና
ሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ትራምፕን “የአብርሃም ስምምነት” ለመቀበል መስማማቷ፣ አሜሪካም ውሎ አድሮ ዕውቅና ልትሰጣት እንደምትችል አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አሜሪካ እውቅና ከሰጠቻት በኃያላኑ አሜሪካ እና ቻይና መካከል አፍሪካ ቀንድ ላይ የጂኦፖለቲካ ፉክክር የሚፈጥር ክስተት ይሆናል።
አሜሪካ እና ቻይና ጂቡቲ ውስጥ የጦር ሠፈር ያላቸው ሲሆን፣ አሜሪካ ቻይና በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ ለመቀነስ ስትል የሶማሊላንዱ በርበራ ወደብ ላይ ሌላ የጦር ሠፈር ለመገንባት ልትፈልግ ትችላለች። ቻይና የሶማሊላንድን መገንጠል ከሚቃወሙት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ሶማሊላንድ በተለይ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማካሄዷእና ለታይዋን እውቅና መስጠቷ አስቆጥቷታል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት ቻይና በሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ላይ ያላት ተቃውሞ ጠንካራ ቢሆንም፣ ፀጥታው ምክር ቤት ግን የአዲስ አገርን ዕውቅና ማጽደቅ አለበት የሚል ሃሳብ በተመድ ቻርተር ውስጥ የለም። ለአንዲት አዲስ አገር ዕውቅና የመስጠት ወይም ያለመስጠት ጉዳይ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚደነግገው ሳይሆን የእያንዳንዱ አገር ፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ ነው።
የፀጥታው ምክር ቤት ሥልጣን ለአዲስ አገር ሕጋዊ ዕውቅና መስጠት ወይም መንሳት ሳይሆን፣ ጠቅላላ ጉባኤው በሚያቀርብለት ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ አዲሲቱ አገር የድርጅቱ አባል እንድትሆን የመቀበልና ያለመቀበል ሥልጣን ብቻ ነው። የድርጅቱ አባል መሆን በድርጅቱ ተቋማት ውስጥ የመሳተፍ እና ድምጽ የመስጠት ዕድል ስለሚፈጥር፣ ይህም ቀላል ሥልጣን አይደለም።