
እንደ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ካሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያገኙ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች፤ እንቅስቃሴያቸው “በንግድ ሥራነት” ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍሉ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ ደንብ፤ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች “ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰርሺፖችን” ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ያገኙትን “ሁሉንም የገቢ መጠን” የሚያሳይ “የሂሳብ መዝገብ” እንዲይዙ ያስገድዳል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ለማይባሉ ወጣቶች የገቢ ምንጭ በሆነው የዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ ላይ ታክስ የሚጣልበት ሁኔታ በዝርዝር የተቀመጠው የገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የገቢ ግብር ረቂቅ ደንብ ነው።
የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የገቢ ግብር ከፋይ ዝርዝር ውስጥ የገቡት ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2017 ዓ.ም. በጸደቀው “የገቢ ግብር አዋጅ” ነው።
አዲሱ ረቂቅ ሕግ፤ በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው። ከአምስት ወራት በፊት የጸደቀው አዋጅ፤ ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ ገቢ የሚያገኝ “አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅቶች” ግብር መክፈል እንዳለባቸው ደንግጓል።
‘የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ’ በሚባለው ዝርዝር ውስጥ እንደ ዩትዩብ እና ቲክቶክ ያሉ “የቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎቶችን” እንዲሁም እንደ ፌስቡክ ያሉ “የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን” ተጠቅመው ገቢ የሚያገኙ ግለሰቦች ተጠቅሰዋል።
“የድምጽ ማስተላለፊያ (ፖድካስት)” እና “የቀጥታ ሥርጭት መድረኮች” ላይ ገንዘብ የሚሠሩ አካላትም እዚህ ውስጥ እንደሚካተቱ አዋጁ ያስረዳል።
ግብሩ የሚከፈለው እነዚህ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች “በኦንላይን መድረኮች ላይ የዲጂታል ይዘትን በመፍጠር እና በማሠራጨት” ከሚያገኙት “ማንኛውም ገቢ” ላይ እንደሆነም ተጠቅሷል። ይህ ገቢ “በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት የሚገኝ” ሊሆን እንደሚችልም ያስገነዝባል።
“ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰርሺፖች” እንዲሁም “የገንዘብ ስጦታዎች እና የብዙኃን የገንዘብ ማሰባሰብ” ግብር ከሚከፈልባቸው የገቢ ምንጮች መካከል ተጠቅሰዋል።
ይዘት ፈጣሪዎች “በማስተዋወቂያ እንቅስቃሴ ምትክ” ከሚያገኟቸው “ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች” እንዲሁም ከሚፈጽሟቸው “የምርት ስም ስምምነቶች እና ድጋፎች” ግብር እንዲከፍሉ በአዋጁ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ግብር የሚከፍሉት ከምን ያህል ገቢ ጀምሮ የሚያገኙ ይዘት ፈጣሪዎች እንደሆነ የተገለጸው ደግሞ አሁን በተዘጋጀው የገቢ ግብር ረቂቅ ደንብ ነው።
ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገንዘብ “የንግድ ሥራ ገቢ” እንደሆነ ተቆጥሮ ግብር እንዲጣልበት የሚያደርጉ ሦስት ሁኔታዎች ረቂቁ ላይ ተቀምጠዋል።
የመጀመሪያው ሁኔታ ከይዘት ፈጣሪዎቹ ዓመታዊ ገቢ ጋር የተያያዘ ነው። የይዘት ፈጣሪው “ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ” ተግባሩ እንደ ‘ንግድ ሥራ ገቢ’ ተቆጥሮ ግብር ይከፈልበታል።
የፎቶው ባለመብት,Getty Images
ይዘት ፈጣሪዎች በዚህ ምድብ ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርገው ሌላኛው ሁኔታ ደግሞ “ግብር ከፋዩ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ወይም ተቀናሽ ወጪ ያለው ከሆነ” የሚል ነው።
ይዘት ፈጣሪዎች በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ገቢ ማግኘታቸው ወይም እንደ ድርጅት አለመቋቋማቸው ግን ከገቢ ግብር ነጻ አያደርጋቸውም።
እነዚህን ሁኔታዎች የማያሟሉ ከሆነ “ሌሎች ገቢዎች” በሚለው ምድብ ውስጥ ገብተው “ከጠቅላላ ገቢያቸው 15 በመቶውን” የመክፈል ግዴታ እንደሚኖርባቸው ባለፈው ዓመት ለጸደቀው አዋጅ የተዘጋጀው ማብራሪያ ላይ ተገልጿል።
“የንግድ ሥራ ገቢ ግብር” የሚለው ምድብ ውስጥ የሚገቡ ይዘት ፈጣሪዎች ከገቢ መረጃ እና መዝገቦች ጋር የተያያዙ ግዴታዎች በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ይጣልባቸዋል።
ይዘት ፈጣሪዎቹ “ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ምንጮች”፤ በዓይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ያገኟቸውን ገቢዎች የተመለከተ “ትክክለኛ እና የተሟላ የሂሳብ መዝገብ” መያዝ ይኖርባቸዋል።
በዚህ የሂሳብ መዝገብ ውስጥ “ከማስታወቂያዎች፣ ስፖንሰርሺፖች፣ ከደንበኝነት ምዝገባዎች እና ከሌሎች ምንጮች የተገኘ ገቢን” የሚያሳዩ መግለጫዎችን ማካተት እንደሚኖርባቸው ረቂቅ ዘርዝሯል። ይህ መግለጫ “ከዲጂታል አገልግሎት መድረኮች የተገኘ” መሆን እንዳለበትም አክሏል።
“ከስፖንሰሮች እና ከማስታወቂያ አቅራቢዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች” እንዲሁም “ክፍያዎችን መቀበልን የሚያሳዩ የባንክ መግለጫዎች” የሚሉትም በሂሳብ መዝገቡ መስፈር ካለባቸው መረጃዎች ውስጥ ናቸው።
“በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ምትክ የተገኙ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች እና ግምታዊ የገበያ ዋጋቸውን” በመዝገባቸው የመያዝ ግዴታም በረቂቁ ሕጉ ይጣልባቸዋል።
ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ያለበት ይህ ረቂቅ ደንብ፤ እስካሁን ድረስ ከታክስ ሥርዓቱ ውጪ ሆነው የቆዩትን ይዘት ፈጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መደበኛው የግብር አሰራር የሚያስገባ ነው።
“ብሩክ ኒውስ” በሚል ስም ቲክቶክ ላይ መረጃዎችን አሳጥሮ በማቅረብ የሚታወቀው ብሩክ ጫላ፤ ይህ እርምጃ “ሲጠብቀው የነበረ” እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የፎቶው ባለመብት,krinfud digitals
“‘መንግሥት ይህንን ጉዳይ እንዴት ሊያስፈጽመው ይችላል?’ የሚለውን ጉዳይ ነበር ያልተረዳሁ” የሚለው ብሩክ፤ በዚህም የተነሳ የሚመጡለትን የማስታወቂያ ሥራዎች አስቀድሞ በመደበኛው መስመር ውስጥ ማስገባቱን ይገልጻል።
“በግሌ የተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎችን እሠራለሁ። ይህንን በምሠራበት ሰዓት ቀጥታ የማስታወቂያ ፈቃድ ነው ያወጣሁት። ይሄ ነገር እንዴት ይዳኛል የሚለው ወደ እኛ መምጣቱ ስለማይቀር […] የማስታወቂያ ፈቃድ አውጥቼ ነበር እየሠራሁ የነበረው” ሲል አስቀድሞ የወሰደውን እርምጃ አስረድቷል።
“የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ማኅበር”ን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ካሉት መሥራቾች አንዱ የሆነው ብሩክ እንደሚገልጸው፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ሥራዎች “አገራችን ላይ ካለው [የሥራ] ዕድል አንጻር ጥሩ ገቢ” ያስገኛል።
የተቋማትን ምርት እና አገልግሎቶች ማስታዋወቅ እንዲሁም በቀጥታ ሥርጭት [ላይቭ] ወቅት የሚሰጡ ‘ወደ ገንዘብ የሚመነዘሩ ጊፍቶች’ ቲክቶክ ላይ ገቢ ከሚገኝባቸው መንገዶች መካከል እንደሆኑ ይጠቅሳል። በይዘት ፈጠራ ገቢ እያገኙ ያሉ ወጣቶች እዚህ ደረጃ ላይ ደረሱት “ሥራ በሌለበት ከባቢ ውስጥ ሆነው [እነዚህን] የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች” በመጠቀም እንደሆነ ያስረዳል።
ብሩክ፤ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ወደ ግብር ሥርዓቱ መግባታቸውን “የሚደግፈው” ጉዳይ ቢሆንም፤ በረቂቁ ላይ በመነሻነት የተቀመጠው የሁለት ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ “በጣም ትንሽ ነው” የሚል ምልከታ አለው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች “ደረሰኝ የማያገኙባቸው” እና “እንደ ወጪ የማይቆጠሩ ተያያዥ ወጪዎች” እንዳሉባቸው ይናገራል።
“በየትኛውም ሚዲያ ላይ የሚንቀሳቀስ ይዘት ፈጣሪ በጣም ብዙ ብዙ የሚባሉ ወጪዎች አሉበት። ከክሪኤቲቪቲ አንጻር ተከታዮችን የሚገነባው በጣም ብዙ ሥራዎችን ሠርቶ ነው። ሁለት ሚሊዮን በጣም ትንሽ ነው” ብሏል።
“ምን አልባት ከፍ ብሎ [በዓመት] ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያገኙ ሰዎችን የግብር ሥርዓቱ ውስጥ ቢገቡ ባይ ነኝ” ሲል የተሻለ የሚለውን አማራጭ ጠቁሟል።