ከመስከረም 2017 እስከ ነሃሴ 2017 በነበረው ጊዜ ውስጥ ኬንያ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት 953 ሕገወጥ የውጭ ፍልሰተኞች መካከል 70 በመቶዎቹ ወይም 670 ያህሉ ኢትዮጵያዊያን ኾነው ተገኙ።
ከኢትዮጵያዊያን ቀጥሎ በብዛት፣ ሶማሊያዊያን፣ ቡሩንዲያዊያንና ኤርትራዊያን ፍልሰተኞች በቅደም ተከተል እንደተቀመጡ የአገሪቱ ጋዜጦች የመንግሥትን እንድ ሪፖርት ጠቅሠው ዘግበዋል።
ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ቁጥር ከፍተኛ የኾነው፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚካሄዱት ግጭቶች እና በትግራይ በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ እንደኾነ ማውሳቱን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኹኔታ፣ ድንበር-ዘለል የጦር መሳሪያና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሠርጎ ገብነት ስጋት መፍጠሩም በሪፖርቱ ተጠቅሷል ተብሏል።