ብሪታንያን፣ ፈረንሳይን፣ ሩሲያንና ቻይናን ጨምሮ 14 የምክር ቤቱ አባላት እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷን አወገዙ

በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸውን ብሪታንያን፣ ፈረንሳይን፣ ሩሲያንና ቻይናን ጨምሮ 14 የምክር ቤቱ አባላት እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷን ትናንት በጉዳዩ ላይ ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አወገዙ። የአሜሪካ ተወካይ በበኩላቸው፣ እስራኤል ከሶማሌላንድ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመስረት መብት እንዳላት ጠቅሠው፣ አሜሪካ ግን የአንዲት ሶማሊያ ፖሊሲዋን እንዳልቀየረች አረጋግጠዋል። ሶማሊያ ባንጻሩ፣ የእስራኤል ውሳኔ ፍልስጤማዊያንን ወደ ሶማሌላንድ ከማስፈር ጋር የተያያዘ ሊኾን እንደሚችል ጠቁማለች። ጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል ውሳኔ ላይ በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲወያይ ጥያቄ ያቀረበችው፣ በምክር ቤቱ ተለዋጭ መቀመጫ ያላት ሶማሊያ ናት። እስራኤል፣ ለሶማሌላንድ የሠጠችው የአገርነት እውቅና በሶማሊያ ላይ የተቃጣ ጠበኛ ድርጊት ተደርጎ መታየት የለበትም ብላለች።