“እባብ ያዬ በልጥ በረዬ” የአርበኛ ዘመነ ካሴ!
በዚህ በእኛ ዘመን ብአዴንን የቀበረ እንጅ ያነበረ ኃይል አልተፈጠረም።አዲሱ ትውልድና አዲሱ አስተሳሰቡ ሁለተኝነትን አይቀበልም።(አዲስ ትውልድ የሚለው አገላለጽ የአስተሳሰብንና የፖለቲካ ርእይን እንጅ እድሜን አይመለከትም። የአማራን ብሔርተኝነትና የህልውና ትግሉን የተቀበለ የ99 ዓመት አንድ አለሙ የሚሰኝ አማራም የአዲሱ ትውልድ አባል ነው።)
እና አዲሱ ትውልድ የማንም ሁለተኛ አይደለም ፥ማንንም ሁለተኛ ማድረግም አይሻም።ተከታይም አስከታም አይደለም። በፍፁም እኩልነትና ፍቅር ያምናል። ማንንም አንበርክኮ በማንም ተንበርክኮ መኖርን ለአንድ ቀን እንኳን አይፈቅድም።
የአማራ ህዝብ ከሌሎች ኃይሎችና ህዝቦች ጋር የመስራት አዝማሚያ ባሳዬ ቁጥር “ተለጠፈ፥ ሁለተኛ ሆነ፥ ጁኔርነት ነው ወዘተ” የሚሉ ራስ ጠል ትርክቶችን መፍጠር ለአዲሱ ትውልድ አይመጥንም። ሰው እንዴት ራሱን ይዘልፋል!?ሰው እንዴት ራሱን በውርደት ጅራፍ ይገርፋል!?
ጁኔርነትን፥ ሁለተኛነትን፥ የመብት ተመጽዋችነትንና ሽራፊ እጣፋንታ ለማኝነትን፥ ብአዴንን ስናስወግድ አነጣጥረን መተን በአንድ ገንዘን ቀብረናቸዋል። ይህን ማረጋገጥ የሚፈልግ ቢኖር ምናልባት እዛ አካባቢ አሁንም ጠረናቸው ይኖራልና ከጠቀመው ሂዶ ይፈልግ።
አንዳንድ ወገኖች “እባብ ያዬ በልጥ በረዬ ”
ሆኖባቸው ልጥ ሲያዩ እባብ መስሏቸው ቢደነግጡ እንረዳለን። የብአዴን ተንበርካኪነት የፈጠረው ጠባሳ አሁንም ግንባራችን ላይ ስላለ መስጋቱ ጤናማ ነው። ከልክ በላይ መፍራት ግን ነውር ነው። እኛ እኮ ጠላቶቻችን እንደ እባብ ቀጥቅጠን ጥለን በዲሽቃ እየቀበርን ያለን ጀግኖች እንጅ የግራር ልጥ ባየን ቁጥር እባብ መስሎን የምንደነግጥ ከንቱዎች አይደለንም።የትም ቦታ ደረታችን ነፍተን ቀና ብለን እንሄድ ዘንድ በደም የተገዛ ክብር አለን። በአደባባይ ቀስቅሰንና ተቀሳቅሰን፥ በአደባባይ አደራጅተንና ተደራጅተን፥ በአደባባይ ታጥቀን፥ በኮረብቶቻችን ስር ጠላቶቻችን ቀብረን በኩራት የቆምን ነን። ሁለተኝነት የተሸናፊዎች እንጅ የእኛ የሸናፊዎች እጣ አይደለም። ጁኒየርነትንና ገባሪነትን እንኳን ለአማራ ህዝብ ለሌሎች ወገኖችም አንመኝም፥ አናወርስም።
ፋኖ የቀይ ባህር ቀጠና አዲሱ የጅኦ ፖለቲካ ኮኮብ እንደሚሆን ዛሬ ሳይሆን ትናንት በቃልም፥በወረቀትም፥ በካሴትም በድፍረትና በርግጠኝነት ስሜት ቀድመን ነግረናል። በአርቲስት ሃብቴ አብረሃም ጉረሮ
“ቀይ ባህር ሰፈር ታዬ አዲስ ኮኮብ፥
ይንቦገቦጋል ሰማይ ሊረከብ።
እንግዲህ አድማስ ተራ በተራ
ገለል በሉለት ለመጭው አውራ።”) ስንል የአማራን ህዝብ መጭ የክብርና የኩራት ዘመን በጥበብ እየገለጽን ነበር።
አንድ ዘመን ያነጠረው ሐቅ አለ! ከዚህ በኋላ ከእኩልነት ውጭ መበላለጥን፥ አንበርካኪና ተንበርካኪነትን እንኳን የኛ የድል አድራጊዎች ትክሻ የኢትዮጵያ መሬት መሸከም አይችልም። ይፈነዳል። ያለነጻነትና ፍትሕ መሬት ተንቀጥቅጦ እንደ ቆርበት ይጠቀለላል፥ አድባር እንደ ቅቤ ይቀልጣል።
ይህን በውል የምንረዳው የአዲሱ ትውልድ አብዮተኞች እኛም አንገብርም ሌላውንም አናስገብርም። አቻ ብቻ!! ሁሉም ህዝቦች አቻ ናቸው።ሁሉም ኃይሎች የሚያስጠብቁት ጥቅም አላቸው። የኛንም አንሰጥም፥ የሌላውንም አንወስድም።አቻ ብቻ!!
ክፋት ለማንም በጎነት ለሁሉም!
አንድ አማራ!
እስከ ምጽአት አማራ!
የአርበኛ ዘመነ ካሴ!