በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት የማዕድን ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰባት ሰዎች ተገደሉ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምእራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት በሦስት የወርቅ እና እምነበረድ ማውጫ ቦታዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተሠማ።

ታጣቂዎች የመጀመሪያውም ጥቃት የፈጸሙት፣ “ቤሮ ማይኒንግ” በተባለ ቦታ በወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ላይ በተሠማሩ የማዕድን አውጪ ኩባንያ ሠራተኞች ላይ መኾኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሁለተኛው ጥቃት አንድ የእምነበረድ ማዕድን ማውጫ ጥበቃዎች ላይ መፈጸሙን የጠቀሠው ዘገባው፣ በጥቃቱ የሁለቱ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አመልክቷል።

ሦስተኛው ጥቃት የተፈጸመው ከእምነበረድ ማውጫው በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ “ሻምበል ሠጠኝ” በተባለ የወርቅ ማውጫ ላይ ሲሆን፣ በዚሁ ጥቃትም ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ተገድለዋል ተብሏል።

በአካባቢው ነዳጅ ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌርም በጥቃቱ መገደሉን ዘገባው ጠቅሷል።

በታጣቂዎች ጥቃቶች የማዕድን ቁፋሮ ንብረቶችን በእሳት የማቃጠል እና የመዝረፍ ድርጊት እንደተፈጸመ ከወረዳው አስተዳደር መስማቱንም የዜና ምንጩ ጨምሮ ዘግቧል። https://miniliksalsawi.substack.com/p/seven-people-killed-in-attacks-on