ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቅሬታ ካሠማ በኁላ ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሳፋሪኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያዎች በቀጠናው በጋራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና የኢንቨስትመንት ትብብሮችን እንዲፈጥሩ እገዛ ለማድረግ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ትናንት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት አስታወቁ። ፕሬዝዳንት ሩቶ፣ በሁለቱ አገራት መካከል የዲጂታል ማስፋፋት እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሠጥተዋል። ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ “ኤም ፔሳ ለሁሉም” የተሰኘው አዲሱ የገንዘብ መገበያያ እና መላላኪያ መተግበሪያ በኢትዮ ቴሌኮም ስልክ ቁጥሮች ላይ እንዳይሠራ እንደታገደበት ገልጦ ቅሬታ ካሠማ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው። በኢትዮጵያ በኩል፣ ሁለቱ መሪዎች በኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ዙሪያ ውይይት ስለማድረጋቸው በወቅቱ አልተገለጠም።