በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅና በእርዳታ አቅርቦት ችግር ከፍተኛ ረሃብ መከሰቱንና በመድኃኒት እጦት ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን መገንዘብ ችለናል። ችግሩ ከሰሞኑ በይፋ ይነገር እንጂ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተመሳሳይ ኹኔታ በሰቆቃ የሚያሳልፉ በርካታ ወገኖቻችን መኖራቸው ይታወቃል። በተለይ በስደተኞች መጠለያ ያሉ፣ በድርቅ ምክንያት ማምረት ያልቻሉ፣ በአጠቃላይ ክልሉ እጅግ አውዳሚ ከኾነ ጦርነት ማግስት ውስጥ መገኘቱና መሰል ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ችግሮች መፈጠራቸው አይቀሬ በመኾኑ ቅድመ ጥንቃቄና ሰብዓዊ ቀውሶች ሲከሰቱ አፋጣኝ መድረሻ የመፍትሔ አማራጮች ማስቀመጥና ከቁጥጥር ውጭ ከመኾናቸው በፊት መድረስ ይገባ ነበር።
አኹን ላይ በተለይ ሕፃፅ በሚባለው መጠለያ ጣቢያ ያሉ ዜጎች በረሃብና መድኃኒት እጦት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው በመኾኑ መላው ኢትዮጵያውያን ተረባርበው የዕለት ጉርሳቸውንና በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ኹኔታ መፍጠር የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ኾኖ አግኝተነዋል።
በትግራይ ያለውን እጅግ የባሰበትና ጊዜ የማይሰጠውን ኹኔታ አነሳን እንጂ ችግሩ በአማራ ክልል ባሉ እንደ ደብረ ብርሃን፣ ጃራ፣… መጠለያ ያሉ ወገኖቻችን በመኖርና በመሞት መሐል ኾነው ቀናቸውን እንደሚገፉ ይታወቃል።
ስለኾነም፣
1. በውጭም በውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን በሚቻለው አቅም ኹሉ ተረባርቦ በረሃብና መድኃኒት እጦት የሚሰቃዩ ወገኖቻችንን እንዲታደጋቸው፣ በዘላቂነትም እንዲያቋቁማቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን።
2. ዓለምአቀፍና ረጂ ተቋማት ለእነዚኽ በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ ላሉ ዜጎች አፋጣኝ እርዳታና ዘላቂ መቋቋሚያ ፕሮጀክቶችን እንዲተገብሩ ተማጽኗችንን እናቀርባለን።
3. የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እነዚኽን ወገኖች የፖለቲካ ቁማር መያዣ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ እርዳታዎችን በቀናነት እንዲያሳልጡ እንዲኹም ወደዳግም ግጭት ከሚገፋ አባባሽ ምክንያቶች እንዲቆጠቡ በአደራ ጭምር እናሳስባለን።
በመጨረሻም እናት ፓርቲ ለእነዚኽ በሰቆቃ ላሉ ወግኖቻችን ለመድረስ በሚደረገው ርብርብ ከዚኽ ቀደም ስናደርግ እንደቆየነው የድርሻችንን እንደምንወጣ ለማሳወቅ እንወዳለን።
እናት ፓርቲ
ታኅሣስ 15/2018 ዓ/ም